በተለያዩ ሃገራት ወቅቱ የጉንፋን ይሆን?
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2017
ኮንጎ ውስጥ የታየው ጉንፋን መሰሉ ህመም
ሰሞኑን ከወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተሰማው ዜና ምንነቱ ባልታወቀ ህመም ከ140 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ያመለክታል። በደቡባዊ ምዕራብ ኮንጎ ክፍለ ሀገር ውስጥ የተከሰተው ይህ በሽታ የጉንፋን ህመም ምልክቶች እንዳሉትትኩሳት እና ከባድ የእራስ ምታት እንደሚያስከትል ነው የተገለጸው። የበሽታውን ምንነት ለማጥናት የህክምና ባለሙያዎች የተሰባሰቡበት አንድ ቡድን ወደ ስፍራው መሰማራቱም ተነግሯል። ታማሚዎቹ ተገቢውን ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው ለሞት መዳረጋቸውን ተከትሎ ስጋት መኖሩን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልጸዋል። የዓለም የጤና ድርጅትም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብሏል።
የብዙዎች ጉንፋን መታመም
ያለንበት ወቅት በተለይ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ጉንፋን የሚስፋፋበትና ብዙዎችም የሚያዙበት ሲያስሉ የሚታይበት ነው። እዚህ ጀርመን በርካቶች ከጉንፋን እና ተያይዞ ከሚመጣው ሳል ጋር ሲታገሉ ይስተዋላል። የበርካቶች መሳል ያሰጋቸው ታዲያ ሕዝብ በብዛት በተሰበሰበት ስፍራ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ በፈቃዳቸው አድርገው ማየቱ ተለምዷል። በተለያዩ ሃገራት የብዙዎች ጉንፋን መያዝ ወረርሽ የተከሰተ አስመስሏል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን አሞኘ በጀርመንና መሰል የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ሃገራት አሁኑ ወቅቱ የጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህም አፍሪቃን ጨምሮ ወደ ደቡቡ ንፍቀ ክበብ አካባቢም ሊዛመት እንደሚችል ገልጸዋል። ምንም እንኳን ብዙዎች በጉንፋን ቢያዙም ወረርሽኝ ተከስቷል ለማለት እንደ የዓለም የጤና ድርጅት ያሉ ከሚመለከታቸው አካል የተሰማ ነገር የለም ይላሉ።
እንዲያም ሆኖ በጉንፋን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ሳይገልጹ አላለፉም። ለዚህም ነው በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ በሚገኙ ሃገራት ለሚፈልጉ ሰዎች የጉንፋን መከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህም ብቻም አይደለም ይላሉ ዶክተር ወንድወሰን በአራተኛነት ጉንፋን የሚያስከትሉ ተሐዋስያንም በቅዝቃዜ ወቅት ስርጭታቸው እንደሚጨምርም ነው የገለጹት። በተለይ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ አካባቢ ከፈረንጆቹ ገና በኋላ ጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ ተባብሶ የመቀጠል ልማድ እንዳለው ያመለከቱት ዶክተር ወንደሰን አውሮጳና አሜሪካ በስፋት መሰራጨቱ ደግሞ ለአፍሪቃም ሊተርፍ የመቻል እድሉ ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።
አንዳንዶች የአየሩን የንጽሕና በተመለከተ አሁን በየቦታው በሚካሄዶ ጦርነቶች የሚተኮሱ ነገሮች ከከባቢው አየር ብክለት ጋር ተዳምሮ መዘዝ ሳያስከትል አልቀረም በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ዶክተር ወንደወሰን የአየር ንብረት ለውጡ ለአየሩ ብክለት አስተዋጽኦው ጉልህ መሆኑ አያነጋግርም ነው የሚሉት።
ጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ
ብዙዎቻችን ጉሮሮ እየከረከረ እራስ ምታትና ትኩሳትን አስከትሎ የህመም ስሜት ሲኖረን በልማድ ጉንፋን አመመኝ ነውየምንለው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ወንድወሰን አሞኘ ጉንፋን የወል ስም መሆኑን ጠቅሰው የጠናው የጉንፋን ዘር በርካቶችን መፍጀቱን አስታውሰዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ወንድወሰን አሞኘ ጉንፋን የወል ስም መሆኑን እና ቀለል ያለ ህመም እንደሆነ የባሰው የጉንፋን ዓይነት ግን ሕይወትን ሊያሳጣ እንደሚችል ነው የተናገሩት።
በታሪክ እንደሚታወቀው ብዙ ሰው የገደለው የኅዳር በሽታ የሚባለው ኢንፍሉዌንዛ 42 ሚሊየን ገደማ ሰዎችን መፍጀቱንም አስታውሰዋል። ኮቪድ ይህን ያህል ሰው አልገደለም በማለትም የቅርቡን የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ያስከተለውን አንስተዋል። ጉንፋን ብለን የምለው ኢንፍሉዌንዛውም ሆነ ሌላው የመተንፈሻ አካላትን የሚያውከውን ህመም እንዴት መከላከል ይቻላል? ሰዎች በየግል በየቤታቸው ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
ዝርዝሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር