የጭንቅላት ዕጢ እና ያለው ህክምና
ማክሰኞ፣ የካቲት 12 2016
በደቡብ ወሎ ደሴ ከተማ እንደሚኖሩ የገለጹ አንድ አድማጭ ፤ «ጤና ይስጥልኝ ዶይቼ ቬለዎች «ወንድሜ ዕድሜው 26 ዓመት ሲሆን የአዕምሮ ዕጢ ህመምተኛ ነው። ህመሙ የጀመረው ከሦስት ዓመት በፊት ነው። መጀመሪያ አካባቢ በእንቅልፍ ላይ እያለ እንደ ትንታ ሳል ያጣድፈዋል ከዚያም ሰውነቱ በሙሉ እንደ ብረት ይወጠራል፤ በከፍተኛ ሁኔታ አካሉ ይንቀጠቀጣል፤ ቆይቶም በአፉ ኮረፋት(አረፋ) የመሰለ ፈሳሽ ይመጣል። ቤተሰብ መጀመሪያ ላይ ከከሰል ጭስ መታፈን ጋር የተያያዘ ነው ብሎ ስላሰበ ብዙም ትኩረት አልሰጠነውም ነበር። ሆኖም ግን ህመሙ ከአንድ ወር በኋላ በድጋሚ ተቀሰቀሰ ከዚህ በኋላ የሚመላለስበት ጊዜም ሲደጋገም ወደ ህክምና ተቋም ወስደን ሲመረመር ነው ህመሙ የተገኘው። ህመሙ በህክምና ከተገኘበት ቀን ጀምሮ እስከ አሁን ማታ ማታ የሚወሰዱ ሁለት ኪኒን እንክብሎችን እየተጠቀመ ይገኛል። እጅግ ያሳሰበን እና ያስጨነቀን ነገር ሀኪሞች በሽታው ከቀዶ ጥገና ውጭ ሌላ የህክምና አማራጭ እንደሌለ ነው የነገሩን። ቤተሰብ ደግሞ ይህን ደፍረን ልንገባበት አልቻልንም። ምክንያቱ ደግሞ ከወንድሜ በፊት በዚሁ በሽታ ተይዘው ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎች መናገርም መንቀሳቀስም ተስኗቸው ተሰቃይተው መሞታቸውን ስለምናውቅ ነው። » በማለት አምስት ጥያቄዎችን ልከውልን ስላሳሰባቸው የጤና ችግር ሁለት የዘርፉን የህክምና ባለሙያዎች አነጋግረናል።
ስለጭንቅላት ዕጢ መንስኤዎች
የጭንቅላት ዕጢ መንስኤያቸው ከማይታወቅ የጤና ችግሮች አንዱ ነው። ሆኖም ለዚህ የጤና ችግር አጋላጭና አባባሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከሚገለጹት መካከል ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ አደገኛ ጨረሮች፣ የቤተሰብ የጤና ሁኔታና ከዘረመል ጋር የተገናኙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። የዘርፉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አብዲ ኤርሞሎ ስለመንስኤው ሲያስረዱ፤ «ብዙውን ጊዜ መላምቶች ናቸው ያሉት» ነው ያሉት። ጥያቄ የተጠየቀላቸው ታማሚ የሚጥል በሽታ እና የሰውነት ማንቀጥቀጥ አይነት እንዳለው በማመልከት በተለያዩ ሰዎች ላይ የተለያዩ የህመም ምልክቶች እንዳሉትም አስረድተዋል።
ዶክተር ፈለቀ ወልደሚካኤል የአእምሮ፣ የአከርካሪ አጥንት እና የነርቭ ቀዶ ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። ስለጭንቅላት ወይም አእምሮ ዕጢ ምንነትና ምልክቶች ሲናገሩ ዕጢው በአንጎል አካል ውስጥ በሽፋኑ እና በአንጎል መላከል እንዲሁም ከአንጎል ውጪ ሊከሰት እንደሚችል ነው ያመለከቱት።
ከባድ እራስ ምታትን ጨምሮ ማስመለስና የተለያዩ ምልክቶችን የሚያስከትለው የጭንቅላት ዕጢ ከእራሱ ከአንጎል ጀምሮ፣ ጭንቅላት ውስጥ ካሉ ዕጢዎች፤ ወይም ወደተለያየ የሰውነታችን ክፍል ከሚሄዱ ነርቮች እንዲሁም ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሊነሳ እንደሚችል ነው የህክምና ባለሙያዎቹ የገለጹት።
የጭንቅላት ዕጢ አይነቶች
አንዳንዶቹ የጭንቅላት ዕጢዎች በወራት ጊዜ ውስጥ ተከስተው በታማሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉ ሲሆኑ መጥፎዎች ብለው ይለዩዋቸዋል የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች። አንዳንዶቹ አይነቶች ደግሞ ቀስ ብለው በረዥም ጊዜ ውስጥ የሚያድጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል። ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ የምርመራው አቅምና የዘርፉም ባለሙያዎች እጥረት ስለነበር ችግሩ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ መሆኑን አሁን ግን የባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን፤ ሀኪም ቤቶችም እንዲሁ ደረጃቸው እያደገ በመምጣቱ የተሻለ የህክምና አገልግሎት መኖሩን ዶክተር አብዲ ገልጸውልናል። ከዚህ በፊት ማይግሬን የሚባለው ከባድ የእራስ ምታት ደጋግሞ የሚያማቸው ወገኖች በደፈናው «እራስ ምታት» ነው ይባል እንደነበር ያመለከቱት ዶክተር አብዲ አሁን እንደ ሲቲ ስካን እና MRI የመሳሰሉ የጭንቅላት ክፍል መመርመሪያዎች መኖራቸው የተሻለ ምርመራ በማድረግ የታማሚዎች የእራስ ምታት መንስኤ ምንነት እንዲታወቅ እየረዳ መሆኑንም አስረድተዋል።
ስለጭንቅላት ዕጢ ህክምና አማራጮች
ህክምናውን በተመለከተ ጠያቂያችን ስጋት አላቸው። ምክንያታቸው ደግሞ ከዚህ ቀደም የቀዶ ህክምና የተደረገላቸው ያጋጠማቸው አሉታዊ ውጤት ነው። ጠያቂያችን ስለጤናው ችግር ከሰጡት ማብራሪያ በመነሳት የአንጎል ዕጢ እንዳለ ግልጽ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ፈለቀ ምንም እንኳን ሀኪም በምርመራ ይህን ቢያረጋግጥላቸውም ስለህክምናው በቀጥታ ምላሽ ለመስጠት ዕጢው የትኛው የአንጎል ክፍል ላይ ነው የመጣው የሚለው መታወቅ እንደሚኖርበት ገልጸውልናል። የሚፈለገው የህክምና አይነትም ዕጢው በጭንቅላት ውስጥ እንደተነሳበት ቦታ ይወሰናል ነው የሚሉት። ዶክተር አብዲም የሚሉት ተመሳሳይ ነው፤ አንድም የዕጢው አይነት ይወስነዋል፤ በዚያም ላይ ክትትል ያስፈልገዋል። የጭንቅላት MRI ምርመራ ክትትል የሚያስፈልገው ከቀዶ ህክምናው በኋላ ዕጢው መተካት አለመተካቱን ለማወቅ እንደሆነም አስረድተዋል። እንደባለሙያው መጥፎው የሚባለው አይነት ከሆነ ተመልሶ የመከሰት ዕድሉ የሰፋ ነው።
ህክምናው በኢትዮጵያ
ጠያቂያችን ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ህክምና በጥሩ ሁኔታ የሚሰጠው የት እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ህክምናው በአሁኑ ጊዜ መሻሻሉን በመግለጹ፤ ሁለቱም የዘርፉ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ፣ ዘውዲቱ እንዲሁም ጴጥሮስ እና አቤት ሆስፒታል ተገቢውን የህክምና እርዳታ ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል። ደሴ ላይም እንዲሁ ሁለት የዘርፉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች መኖራቸውንም ነግረውናል። ዶክተር አብዲ ቦታዎቹን ከመጠቆም አልፈው እንደውም ወደ አዲስ አበባ መሄድ ከቻሉ እሳቸው በዚህ የህክምና ዘርፍ በኃላፊነት በሚያገለግሉት በጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቢሄዱ ሊያማክሯቸው ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸውልናል። ለጠያቂያችን ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን የህክምና ባለሙያዎች ከልብ እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ