1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ ጦር ከኒዤር ለቅቆ እንዲወጣ ተገደደ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 2016

ፈረንሳይ ጦሯን ከምዕራብ አፍሪቃዊቷ ኒዤር ለማስወጣት ተገድዳለች ። በኒዤር ከሁለት ወራት በፊት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው ኃይል የፈረንሳይ ጦርን ከሀገሪቱ መውጣት ለኒዤር ሉዓላዊነት አዲስ ጅማሬ ብሎታል ። የፈረንሳይ ጦር በቻድና ካሜሩን በኩል ወደብ ለመድረስ 3 ሺሕ ኪሎ ሜትር አስቸጋሪ የምድር ጉዞ ይጠበቅበታል።

https://p.dw.com/p/4XWKr
የፈረንሳይ ጦር ከኒዤር ለመውጣት ተገድዷል
የፈረንሳይ ጦር ከኒዤር ለመውጣት ተገድዷል ። 1,500 የፈረንሳይ ጦር በቻድና ካሜሩን አሳብሮ ወደ ወደብ ለመድረስ 3 ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት በአስቸጋሪ ሁኔታ መጓዝ ይጠበቅበታል ።  ምስል Dominique Faget/AFP

በምዕራብ አፍሪቃ ፀረ ፈረንሳይ ንቅናቄና ጥላቻ በርክቷል

ፈረንሳይ በቀድሞ የአፍሪቃ ቅኝ ግዛቶቿ ላይ የነበራት ቀጥተኛ ወታደራዊ ተጽእኖ እና ተሳትፎ ቀስ በቀስ እየከሰመ የመጣ ይመስላል ።  በተለይ በኒዤር ከሁለት ወራት በፊት ወታደራዊ ሁንታው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሞሐመድ ባዞምን በመፈንቅለ መንግሥት ካስወገደ በኋላ የፈረንሳይ በአፍሪቃ ቀጥተኛ ወታደራዊ ተሳትፎ እያከተመ ነው ። የኒዤሩ መፈንቅለ መንግሥት ላለፉት 3 ዓመታት በመካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ ከተከናወኑ መፈንቅለ መንግሥታት ስምንተኛው መሆኑ ነው ።

ባለፈው ሳምንት ሰኞ በዋና ከተማዪቱ ኒያሚ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የፈረንሳይ ጦር ከሀገራቸው ለቅቆ እንዲወጣ በአደባባይ ሰልፍ ጠይቀዋል ። በኒዤር መፈንቅለ መንግሥቱ ከተደረገ ከሁለት ወራት በኋላም ፈረንሳይ ጦሯን ማስወጣት ጀምራለች ። የነዋሪዎቹ ጥሪ ምላሽ ማግኘት ይገባው እንደነበር አንድ የኒያሚ ነዋሪ ተናግረዋል ።

የሕዝቡ ጸረ ፈረንሳይ ንቅናቄና ጥላቻ

«የኒዤር ሕዝብ በአጠቃላይ የሆነ ኃይል መውጣት አለበት ብሎ ከወሰነ፤ ኃይል መውጣት አለበት ደግሞ የሕዝቡ ፍላጎት ነው   የሕዝብ ፍላጎት ሁሌም ሊከበር ይገባል »

የፈረንሳይ እና የጀርመንጦርን ጨምሮ የምዕራባውያኑ ወታደሮች ቀደም ሲል ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተከናወኑባቸው የኒዤር ጎረቤቶች፦ ማሊ እና ቡርኪናፋሶም ለቅቀው ለመውጣት መገደዳቸው የሚታወስ ነው ። ከቅርብ ጊዜያት አንስቶም በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ፀረ ፈረንሳይ አቋሞች እና ጥላቻዎች ሲንጸባረቁ ተስተውለዋል። 

የፈረንሳይ ጦር ወታደር በኒዤር
የፈረንሳይ ጦር ወታደር በኒዤር፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Dominique Faget/AFP

ኒዠር የዓለም ኃያላን የእጅ አዙር መፋለሚያ

ፈረንሳይ ኒዤር የሠፈሩ ከ1,500 በላይ ወታደሮችዋን ካለፈዉ ማክሰኞ ጀምሮ ከምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ማስወጣት የጀመረችው ከኒዤር ወታደራዊ ሁንታ ከፍተኛ ግፊት ስለተደረገባት ነው ። በእርግጥ የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ ጦራቸውን ከኒዤር እንደሚያስወጡ ከተናገሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል ። የፈረንሳይ ጦር ከኒዤር ለቅቆ መውጣቱን ወታደራዊ ኹንታው ለኒዤር ሉዓላዊነት አዲስ ጅማሬ ብሎታል ።

የፈረንሳይ ጦር በ3 ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት የምድር ጉዞው ብርቱ ፈተና ተደቅኖበታል

ከኒዤር የሚወጡ የፈረንሳይ ወታደሮችየጦር መሣሪያዎቻቸውን በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ሲወጡ ወደብ እስኪደርሱ የቻድ ጦር ኃይል ያጅባቸዋል ተብሏል ። ጦር ሠራዊቱ ፈረንሳይ ለመድረስ ከኒዤር ከወጣ በኋላ በቻድ፣ በካሜሩን በኩል አቋርጦ ወደብ ለመድረስ 3 ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት በአስቸጋሪ ሁኔታ መጓዝ ይጠበቅበታል ።  ከኒዤር በወታደራዊ አውሮፕላኖች መውጣት የቻሉት ጥቂት የፈረንሳይ ወታደራዊ መኮንኖች ብቻ ናቸው ። የፈረንሳይ ጦር የሚጓዝበት ቀጣና የፈረንሳይ ጦር ከዚህ ቀደም ሲወጋቸዉ የነበሩ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊዎች የሸመቁበት ሊሆን ስለሚችል ለፈረንሳይ ጦር ጉዞውን አደገኛ እና አስቸጋሪ እንደሚያደርግበትም ተጠብቋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ