1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኒዠር የዓለም ኃያላን የእጅ አዙር መፋለሚያ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13 2015

​​​​​​​የኒዠር የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙምን ከሦስት ሳምንት በፊት በኃይል ከሥልጣን አዉርዶ መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኹንታ ለምዕራባውያን በተለይ ለፈረንሳይ ሙሉ ለሙሉ ጀርባውን ሰጥቷል ። በአንጻሩ ከምዕራባውያን ጋር በዩክሬን ጉዳይ የምትወዛገበው ሩስያ ለወታደራዊ ኹንታው ድጋፏን ዐሳይታለች ። ፍጥጫው ወዴት ያመራ ይሆን?

https://p.dw.com/p/4VKqH

ኤኮዋስ በኒዤር ጉዳይ ከማስጠንቀቂያ አልዘለለም

Nigeria  Abuja | ECOWAS Treffen Verteidigungsminister
ምስል Chinedu Asadu/AP Photo/picture alliance

ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙምን ከሦስት ሳምንት በፊት በኃይል ከሥልጣን አዉርዶ መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኹንታ ለምዕራባውያን በተለይ ለፈረንሳይ ሙሉ ለሙሉ ጀርባውን ሰጥቷል ። በአንጻሩ ከምዕራባውያን ጋር በዩክሬን ጉዳይ የምትወዛገበው ሩስያ ለወታደራዊ ኹንታው ድጋፏን ዐሳይታለች ። እንደውም ማናቸውም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶችን በቀላሉ እንደማታይ ዐሳውቃለች ። ኤኮዋስ በኒዠር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመመለስ ወታደራዊ ርምጃ እወስዳለሁ ሲል ያስቀመጠው ቀነ ገደብ የተጠናቀቀው ባለፈው ሳምንት ነው ። ፍጥጫው ወዴት ያመራ ይሆን?  

ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙምን በወታደራዊ ኃይል ከሥልጣን ያስወገደው የኒዠር ቀውስ ሩስያ እና ምዕራባውያንንም አፍሪቃ ምድር ውስጥ በእጅ አዙር አፋጥጧል ። የአውሮጳ ኅብረትን ጨምሮ ምዕራባውያን መፈንቅለ መንግሥት ፈጻሚ የኒዠር ወታደራዊ ኹንታን ከማውገዝም በላይ ማስጠንቀቂያ እየሰነዘሩ ነው ። በዚያው ልክ የኒዠር መፈንቅለ መንግሥት አጋጣሚን በአፍሪቃ ተጽእኖዋን ለማሳደር እንደ መልካም አጋጣሚ ያየችው ሩስያ፦ በኒዠር ላይ የሚሰነዘር ማናቸውንም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በቀላሉ እንደማትመለከት ዐስታውቃለች ።

ኒጀር ዋና ከተማ ኒያሜይ፤ ወታደራዊ ኹንታውን በመደገፍ የተደረገ ሰልፍ ።
ኒጀር፤ ኒያሜይ፤ ወታደራዊ ኹንታውን በመደገፍ የተደረገ ሰልፍ ። የማሊ እና ቡርኪናፋሶ መሪዎችም ለኒጀር ወታደራዊ ኹንታ ድጋፋቸውን ገልጠዋል ። ሰልፍ አድራጊዎች ካናቲራቸው ላይ የኒጀር፤ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ወታደራዊ ኹንታዎችን እንደሚደግፉ በምስል አስደግፈው ዐሳይተዋል ። ምስል AFP

የኤኮዋስ ማስጠንቀቂያ

በቅርቡ ወታደራዊ ኹንታ የተካሄደባት ኒዠር ቀውስ ያሳስበኛል ያለው የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ (ECOWAS) በበኩሉ በመከላከያ ሚንሥትሮቹ በኩል ጋና ውስጥ የሁለት ቀናት ጉባኤ ሐሙስ እና ዐርብ አካሂዷል ። አማራጮች ሁሉ ከከሸፉ ኤኮዋስ በኒዠር ወታደራዊ ጣልቃ እንደሚገባ ም አስጠንቅቋል ። ከጉባኤው ቀደም ብሎ የናይጀሪያ መከላከያ ሚንስትር ጄኔራል ክሪስቶፈር ግዋቢን  መፈንቅለ መንግሥቱን እንዲህ አውግዘዋል ።

«ኒዠር ሪፐብሊክ ውስጥ የተከሰተው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለኤኮዋስ ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሴያዊ እሴቶች፤ በሀገር መረጋጋት ብሎም በሕግና ስርዓት መስፈን ሁሉ ለሚያምኑ ብርቱ ስጋት ነው ። ድርጊቱ በቀጣናችን የገጠመን አሳዛኝ ተግዳሮት ነው ። በጋራ መቆም እና አንድነት እጅግ እንደሚያስፈልገንም አመላካች ነው ። ዛሬ ይህን ንግግር በምናሰማበት ወቅት፤ ለሁላችንም ማስታወስ የምፈልገው የመሰብሰባችን ምክንያቱ አንዳች ክስተት ላይ ምላሽ ለመስጠት ብቻ አይደለም ። ይልቁንስ   ሰላም እና መረጋጋቱን በማስጠበቅ በቀጣናው ዴሞክራሲያዌ መርኆች እና መረጋጋቶች እንዲጎለብቱ  ለማበረታታት ነው ።»

የኤኮዋስ ጄነራሎች አስቸኳይስብሰባ በጋና

ጋና የተሰበሰበው ኤኮዋስ እንደ አስፈላጊነቱ  «ተወርዋሪ ኃይሉን» በተጠንቀቅ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሷል ።
በጄኔራሎቹ በኩል ሐሙስ ነሐሴ 11 እና ዐርብ ነሐሴ 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ጋና ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ደረገው ኤኮዋስ እንደ አስፈላጊነቱ  «ተወርዋሪ ኃይሉን» በተጠንቀቅ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። አማራጮች ሁሉ ከከሸፉ ኤኮዋስ በኒዠር ወታደራዊ ጣልቃ እንደሚገባአስጠንቅቋል ። ምስል Richard Eshun Nanaresh/AP Photo/picture alliance

ትናንት እና ከትናንት በስትያ ኤኮዋስ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ  «ተወርዋሪ ኃይሉን» በተጠንቀቅ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። የጋና መከላከያ ሚንሥትር ዶሚኒክ ኒትዊል ለተሰብሳቢ ጄነራሎቹ ቀጣዩን መልእክት አስተላልፈዋል።

«የተወደዳጅሁ ጄነራሎች፦ እናንተ እና የእናንተ ታማኝ ትጉኃን ወታደሮች ዛሬ በታሪክ አጋጣሚ የምዕራብ አፍሪቃ ሕዝብ መሪዎቹን በነጻ እና ፍትሐዊ አጠቃላይ ምርጫዎች  መምረጥ እንዲችል ለማድረግ ኃላፊነት ተደቅኖባችኋል ። »

ኢኮዋስ የኒዠርን ዴሞክራሲ ለመመለስ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እፈጽማለሁ ሲል ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀበት ወቅት መንበረ-ሥልጣኑን በኃይል የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኹንታ የሀገሪቱን የአየር ክልል የዘጋው ወዲያው ነበር ።

ጋና የተሰበሰበው ኤኮዋስ እንደ አስፈላጊነቱ  «ተወርዋሪ ኃይሉን» በተጠንቀቅ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሷል ።
በጄኔራሎቹ በኩል ሐሙስ ነሐሴ 11 እና ዐርብ ነሐሴ 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ጋና ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ደረገው ኤኮዋስ እንደ አስፈላጊነቱ  «ተወርዋሪ ኃይሉን» በተጠንቀቅ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። አማራጮች ሁሉ ከከሸፉ ኤኮዋስ በኒዠር ወታደራዊ ጣልቃ እንደሚገባአስጠንቅቋል ። ምስል Francis Kokoroko/REUTERS

የኒዤር ወታደራዊ ኹንታን በመቃወም የተሰጡ አስተያየቶች

በወታደራዊው ኹንታ ቁጥጥር ከቤተሰባቸው ጋር ቤተመንግሥት ውስጥ ታስረው የሚገኙት የ63 ዓመቱ የኒዤር የቀድሞ ፕሬዚደንት ሞሐመድ ባዙም የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ነው ተብሏል ። የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሻርልስ ሚሼል፦ የቀድሞው  የኒዤር ፕሬዚደንት ሕክምና ሊያገኙ ይገባል ሲሉ ዐርብ ዕለት አሳስበዋል ። ጉዳዩ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችልም ወታደራዊ ኹንታውን አስጠንቅቀዋል ።

የጋናው መከላከያ ሚንስትር ምዕራብ አፍሪቃ ላይ የተደቀነውን ሥጋት እንዲህ ገልጠውታል ።  

«በጊኒ እና በኒዤር የፕሬዚደንት ጠባቂዎች፤ ቃሉን ልጠቀም እና ፕሬዚደንቶቻቸውን የሚያግቱ ከሆነ  ማንም ቢሆን ልደገመው ማንም ቢሆን በምዕራብ አፍሪቃ ከስጋት ውጪ አይሆንም።»

ጋና የተሰበሰበው ኤኮዋስ እንደ አስፈላጊነቱ  «ተወርዋሪ ኃይሉን» በተጠንቀቅ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሷል ።
በኤኮዋስ አስቸኳይ ስብሰባ፦ አብደል-ፋታው ሙሳህ የኤኮዋስ ኮሚሽነር ተሳታፊ ሆነዋል ። ጋና የተሰበሰበው ኤኮዋስ እንደ አስፈላጊነቱ  «ተወርዋሪ ኃይሉን» በተጠንቀቅ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሷል ።ምስል Richard Eshun Nanaresh/AP/dpa/picture alliance

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የሰብአዊ መብቶች ኃላፊ ፎልከር ቱርክ ዐርብ ዕለት፦ መፈንቅለ መንግስቱን በብርቱ አውግዘዋል ። «ኒዤር ውስጥ እጅግ አስፈላጊው ነጻነት አደጋ ላይ ወድቋል»ም ብለዋል ።

ኒዠር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1960 ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻነቷን ካወጀች በኋላ በቅርቡ ያስተናገደችው መፈንቅለ መንግሥት በታሪኳ አምስተኛው ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ