1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት የአፈጻጸም ግምገማ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6 2016

በአመዛኙ በጎ ነበር በተባለው የዚህ የስትራቴጂካዊ ግምገማ ውይይት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ዘላቂ ድጋፍ እንደሚያደርግ የአፍሪካ ሕብረት አቋሙን ያሳየበት እንደነበርም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4iFb3
Äthiopien Friedensabkommen Tigray
ምስል PHILL MAGAKOE/AFP/Getty Images

የፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት የአፈጻጸም ግምገማ 

 

የአፍሪካ ሕብረት ያስተናበረው የፕሪቶሪያው የዘላቂ ተኩስ ማቆም ስምምነት ሁለተኛ ዙር ግምገማ በስምምነቱ ፈራሚዎች - የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ሕወሓት እንዲሁም ታዛቢዎች መካከል አዲስ አበባ ላይ ተደርጓል።

የግምገማው አላማ ስምምነቱ እስካሁን ያስገኛቸው በጎ ሥራዎችን ለማስቀጠል እና የተስተዋሉ ችግሮችን ለማረም፣ በዘላቂነት የስምምነቱን አተገባበር ስኬታማነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ስልቶችን ለመንድፍ መሆኑንየአፍሪካ ሕብረት ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ኃላፊ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር እና በአፍሪካ ቀንድ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጋር መወያየታቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።

በስምምነቱ ግምገማ ውይይት የተዳሰሱ ጉዳዮች

ሰሜን ኢትዮጵያን ክፉኛ ያደቀቀውን ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ትምምን እና የፊርማ ስምምነት፣ ሁለተኛው ዙር የአፈፃፀም ግምገማ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ግቢ ውስጥ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. መካሄዱን ሕብረት አስታውቋል።

በግምገማው ከስምምነቱ ፈራሚዎች በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ሕብረት በታዛቢነት መሳትፋቸውም ተነግሯል። በዚህ ሂደት ለስምምነቱ አወንታዊ ሚና ነበራቸው የተባሉት ጎረቤት ሀገር ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ መሳተፋቸውም በወጣው መግለጫ ተገልጿል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀደመ ቀያቸው የመመለስ፣ የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተን እና ወደ ማሕበረሰቡ መልሶ ማዋሃድን የተመለከቱ ቁልፍ  ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል ተብሏል። ይህንን ማስፈፀም የሚቻልበት የመልሶ ግንባታ ማስኬጅያ የገንዘብ ድጋፍ  ጉዳይም ከውይይቱ ነጥቦች መካከል እንደነበሩ ሕብረቱ አስታውቋል።

የፕሪቶሪያ ውል ፈራሚዎችና አደራዳሪዎች
የፕሪቶሪያ ውል ፈራሚዎችና አደራዳሪዎችምስል PHILL MAGAKOE/AFP

ሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚ አካላት - የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ለውይይት በቀረቡት ጉዳዮች ዙሪያየአፈፃፀም መሻሻል ስለመኖሩ እውቅና ሰጥተው ቀሪ ሂደቶችን ቀስ በቀስ በታሰበው መጠን ለመፈጸምም ትምምን ላይ መድረሳቸው የተነገረ ሲሆን፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ይህንኑ በ ኤክስ መገናኛ ዐውታር አረጋግጠዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት መሻሻል እንዳለ ሁለቱም አካላት ስለመቀበላቸው ጽፈዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በዚህ የስምምነቱ አተገባበር ግምገማ ውይይት ላይ ሕወሓት ዳግም ሕጋዊ ሕልውናውን ስለሚያገኝበት የምዝገባ ሁኔታ እንዲሁም፣ ሱዳን ውስጥ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ለጥቃት ተጋላጭ እየሆኑ ይገኛሉ ስለተባሉ የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ ምክክር መደረጉንም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት የፌደራሉ መንግሥት እና ሕወሓት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ላስመዘገቡት የተሻሻለ ሒደት እንዲሁም ስምምነቱን እየተከታታሉ ያሉ አባላት ላሳዩት በጎ ክትትል ምስጋና ማቅረባቸውም ተነግሯል።

የፕሪቶሪያ ውል ሲፈረም
የፕሪቶሪያ ውል ሲፈረምምስል Themba Hadebe/AP/picture alliance

በአመዛኙ በጎ ነበር በተባለው የዚህ የስትራቴጂካዊ ግምገማ ውይይት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ዘላቂ ድጋፍ እንደሚያደርግ የአፍሪካ ሕብረት አቋሙን ያሳየበት እንደነበርም ተገልጿል። ይህም የተባለው ሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚዎች ለሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ገለጻ ካቀረቡ በኋላ ስለመሆኑ ተነግሯል። 

የፌደራል መንግሥት በዚሁ ጉዳይ ላይ እስካሁን ምንም ያለው ነገር የለም። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዓመቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻ ጉባኤ ላይ ለምክር ቤት አባላት ባለፈው ሳምንት በሰጡት ማብራሪያ የስምምነቱ አፈፃፀም በጥሩ ውጤት ገቢራዊ እየሆነ ስለመሆኑ ገልፀው ነበር።

በአፍሪካ ሕብረት ሥር የተካሄደው የፕሪቶሪያው ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት የመጀመሪያ ዙር ግምገማ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር እዚህ አዲስ አበባ የተካሄደው።

የተሃድሶ ኮሚሽን እና የአሜሪካ ባለስልጣናት ውይይት

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እና ወደ አዲስ አበባ በተደጋጋሚ ጊዜ ከሚመጡት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ጋር መወያየታቸው ተነግሯል።

የአሜሪካ ኤምባሲ በምስል አስደግፎ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ እነዚህ አካላት በፕሪቶሪያው ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ በመበተን እና መልሶ በማዋሃድ ሒደት ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች "ዘላቂ" የተባለ ሰላም እንዲሰፍን ለማገዝ አሁንም ቁርጠኛ መሆኗን ስለመግለጿ ኢምባሲው ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር