የፖሊ-ጂሲኤል የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እና ልማት ለምን መከነ?
ረቡዕ፣ መስከረም 18 2015ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን በያዙ በሶስተኛው ወር ገደማ ኢትዮጵያ ድፍድፍ ነዳጅ ለማውጣት መዘጋጀቷን የሚያበስር የምስራች ይዘው ብቅ አሉ። አገሪቱ ለበርካታ አስርት ዓመታት ያስፈለገችውን ነዳጅ ለማውጣት መብቃቷ እና ወደ ጅቡቲ የሚዘረጋው ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዣ ዐቢይ ተስፋ የጣሉባቸው ነበሩ። "በአንድ በኩል ወደ አገር ውስጥ የምናስገባውን ነዳጅ በሀገር ውስጥ ምርት ማሟላት ከቻልን ለዚያ የምናወጣውን የውጪ ምንዛሪ እንድንቀንስ ያደርጋል" ያሉት ዐቢይ ተሳክቶላት ኢትዮጵያ ነዳጅ ወደ ውጪ መላክ ከቻለች "አዲስ የውጪ ምንዛሪ ማግኛ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል" ብለው ነበር።
ዐቢይ የምሥራቹን በተናገሩ በማግስቱ ማለትም ሰኔ 21 ቀን 2010 በሶማሌ ክልል ጎዴ ኢላላ በተባለ ቦታ የቻይናው ፖሊ ሲጂኤል ኩባንያ ድፍድፍ ነዳጅ ማውጣት በይፋ ሲጀምር በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኙ። የቻይናው ኩባንያ አርማ ያረፈባቸው ባርኔጣዎች በጭንቅላታቸው ጣል ያደረጉት ባለሥልጣናት በአነስተኛ ጠርሙስ የድፍድፍ ነዳጁን ናሙና በእጃቸው ከፍ አድርገው በመያዝ ደስታቸውን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ጋዝ ልማት ስንት ታገኝ ይሆን?
ይኸ ዜና ለበርካታ አስርት ዓመታት በኦጋዴን ሸለቆ ሲደረግ የቆየው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ በመጨረሻ ፍሬ ሊያፈራ ተቃረበ የሚል ተስፋ የሰጠ ነበር። ከፖሊ-ጂሲኤል በፊት የሩሲያ፣ የዮርዳኖስ፣ የቻይና እና የማሌዥያ ኩባንያዎች ሞክረው አልተሳካላቸውም። ፖሊ-ጂሲኤል የቻይና መንግሥት ንብረት የሆነው ቻይና ፖሊ ግሩፕ ኮርፖሬሽን እና መቀመጫውን በሖንግ ኮንግ ያደረገ ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የተባለ የግል ኩባንያ በጥምረት ያቋቋሙት ነው።
ኩባንያው በካሉብ እና ሒላላ ከሚያከናውነው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እና ልማት በተጨማሪ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ መንግሥታት በተፈራረሙት ውል መሠረት እስከ ጅቡቲ የ767 ኪሎ ሜትር የተፈጥሮ ማጓጓዣ የመገንባት ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር። በጅቡቲ ወደብ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (Liquefied natural gas) ማቀነባበሪያ መገንባት የሚጨምረው ይኸ ሥራ ግን እስከ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከፍተኛ ተስፋ የጣሉበት እና በፖሊ-ጂሲኤል አማካኝነት ሲከናወን የቆየው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ግን በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የጤና እክል አስከትሏል የሚል ውንጀላ ይቀርብበታል። የሶማሌ ክልል ኖጎብ ዞንን በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ኡሳም መሐመድ ኩባንያው ኬሚካል ያጓዘባቸው ጀሪካኖች ወደ አካባቢው ነዋሪዎች እጅ በመግባታቸው የጤና እክል ማስከተሉን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ኡሳም "ይኸ ጤናቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቷል። እስካሁን ወደ ሆስፒታል የሚያመጧቸው ልጆች አሉ። እጅግ በጣም የታመሙ፤ አይናቸውን ያጡ አሉ" ሲሉ ተናግረዋል። የብሪታኒያው ዘጋሪዲያን ጋዜጣ ፖሊ-ጂሲኤል ሥራውን በሚያከናውንበት አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን እስከ ሞት ያደረሰ ምንነቱ ያልታወቀ ህመም መከሰቱን ከሁለት ዓመታት በፊት ዘግቧል። ዶይቼ ቬለ ከሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት እና ከማዕድን ሚኒስቴር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
የፖሊ ጂሲኤል የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋም ሆነ ወደ ጅቡቲ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዣ ቧንቧ ግንባታ ባለፉት አራት ዓመታት በታቀደው ፍጥነት አልተጓዘም። ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ዑማ የጠቀሷቸው ጉዳዮች በፖሊ ጂሲኤል ኩባንያ እና በኦጋዴን ሸለቆ በሚያከናውነው ሥራ መንግሥታቸው የሰነቀው ተስፋ ብን ብሎ መጥፋቱን የሚያሳብቁ ነበሩ።
"ኩባንያው ፈቃድ ወስዶ በነበረባቸው ዘጠኝ ዓመታት የሚጠበቅበትን ሥራ ያላከናወነ መሆኑ በግምገማ ተረጋግጧል" ያሉት አቶ ታከለ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ "መንግሥት እና ሕዝብ ከፍተኛ ተስፋ የጣለበትን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት በተያዘለት ጊዜ እውን እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥሯል" ብለው ነበር። ሚኒስትሩ "ኩባንያው ያለበትን የፋይናንስ እና የቴክኒክ አቅም ውስንነት እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ካላሟላ ሥምምነቱ የሚቋረጥ ስለመሆኑ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል" በማለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።
ለፖሊ ጂሲኤል የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ግን የፈየደው ነገር የለም። ከዘጠኝ ዓመታት ጥበቃ በኋላ በስተመጨረሻ የኢትዮጵያ መንግሥት ለቻይናው ፖሊ ጂሲኤል የሰጠውን የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እና ልማት ፈቃድ ባለፈው ሣምንት አቋርጧል። መስከረም 11 ቀን 2015 ውሳኔውን ይፋ ሲያደርጉ መንግሥታቸው ለኩባንያው ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሱት የማዕድን ሚኒስትሩ "በተለያየ ጊዜ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎችም ብንሰጣቸው ሊያሳኩት ስላልቻሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበራቸው የፍለጋ እና የልማት ውል አቋርጠናል" ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ ታከለ ኩባንያው ሥራውን ለማከናወን የፋይናንስ እና የቴክኒክ አቅም እንደሌለው በዕለቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ ፖሊ ጂሲኤል እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም። ዶይቼ ቬለ አዲስ አበባ ከሚገኘው የፖሊ ጂሲኤል ጽህፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም። ፖሊ ጂሲኤል "የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጋዝ እና ድፍድፍ ዘይት ለማልማት የሚያበቃ" የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የቴክኒክ አቅም ካበጀ "መንግሥት ተቀብሎ ለማሰራት ዝግጁ" መሆኑን አቶ ታከለ ዑማ ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ኡሳም መሐመድ ለበርካታ አስርት ዓመታት በአካባቢው ሲካሔድ የቆየው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ "ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይም ቁፋሮ በሚካሔድበት አካባቢ ለሚገኘው ግልጽ አይደለም" ሲሉ ይተቻሉ። ከሚገኘው ጥቅም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምን ያክል ይደርሳል? ኩባንያዎቹ ሊያከብሩ የሚገባቸው የጤና፣ አካባቢያዊ እና ማኅበራዊ ደረጃዎች የትኞቹ ናቸው የሚሉ ጉዳዮች ምላሽ እንደሚያስፈልጋቸው የሚናገሩት አቶ ኡሳም ከአርብቶ አደሩ አኗኗር ጋር ጭምር ማስማማት እንደሚያሻ ያስጠነቅቃሉ።
"አገሪቱ የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ኩባንያዎቹ እንዴት መተባበር እንዳደሚችሉ መላ ማበጀት ያስፈልጋል" ያሉት አቶ ኡሳም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ግልጽ የሆነ ገቢ መፍጠር፣ የጤና እና የልማት መሠረት ልማቶች ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል። አቶ ኡሳም እንደሚሉት "ከዚህ በተጨማሪ የውሳኔ አሰጣጡ ሒደት የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሚያካትት ሊሆን ይገባል።"
በኢትዮጵያ የተሰማራበት የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እና ልማት ሥራ የመከነበት ግን ፖሊ ጂሲኤል ብቻ አይደለም። ጂፒቢ የተባለ የሩሲያ ኩባንያ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት በ2014 በራሱ ፈቃድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተፈራረመውን ውል እንዳቋረጠ የማዕድን ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ሪፖርት ያሳያል። ኒውኤጅ የተባለ የብሪታኒያ ኩባንያ "ግዴታውን መወጣት ባለመቻሉ ለበርካታ ጊዜያት ማራዘሚያ ቢሰጠውም መስራት ሳይችል የስምምነት ጊዜው" መጠናቀቁን የማዕድን ሚኒስቴር ገልጿል።
አቶ ታከለ ዑማ የሚመሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በኦጋዴን ሸለቆ የሚገኘውን የነዳጅ ሐብት መጠን እና የኤኮኖሚ አዋጭነት በአሜሪካ ኩባንያ አስጠንቶ የማረጋገጫ ሰርተፍኬት ተቀብሏል። ሥራውን ያከናወነው በነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ኔዘርላንድ ስዉል ኤንድ አሶሼትስ የተባለ ኩባንያ ነው።
የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ታከለ ዑማ ኩባንያው "አራት ወር ወስዶ በትንሹ በሶስት ጉድጓድ እና እዚያ አካባቢ ያለው ወደ 7 ትሪሊዮን ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ እና ከዚህ በፊት ያልሰማንው የትኛውም ኩባንያ ያልነገረን ድፍድፍ ዘይት እንዳለ" መግለጹን አስረድተዋል።
የኔዘርላንድ ስዉል ኤንድ አሶሼትስ ኩባንያ ምክትል ፕሬዝደንት ጆሴፍ ውልፍ ሰነዱን ለማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ታከለ ዑማ ባለፈው ነሐሴ ሲያስረክቡ የተቋማቸው ሪፖርቶች "በፋይናንስ ኢንዱስትሪው እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የኩባንያዎችን ድርሻዎች በአክሲዮን ገበያዎች በሽያጭ ለማቅረብ፣ ከባለወረቶች ተጨማሪ ፋይናንስ ለማሰባሰብ እና በተቋማት ድርሻዎችን ለመግዛት ጥቅም ላይ" እንደሚውሉ ጠቁመዋል። "ይኸንን ለባለወረቶች ስታቀርቡ ተዓማኒነት ያገኛል" ያሉት ጆሴፍ ውልፍ ሪፖርቱ "ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ጋዝ እና የነዳጅ ዘይት ፍላጎት ለማሟላት ያላትን እምቅ አቅም ሰንዷል" ሲሉ ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ