1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጅምላ እስር፤ ተመድ፤ ብሪክስና የኑሮ ውድነት

ዓርብ፣ ነሐሴ 26 2015

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ስለ ጅምላ እስሩና ሰብአዊ መብት ጥሰቱ የሰጠው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ እጅግ ያሻቀበው የሸቀጦች ዋጋና የኑሮ ውድነት፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ስለመጋበዟ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል ። በድምፅም በጽሑፍም ከታች ይገኛል ።

https://p.dw.com/p/4Volg
የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ ። አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ ። በዋና ከተማዪቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በዋናነት የአማራ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስር መደረጉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት እጅግ አሳሳቢ ብሎታል ። ምስል Seyoum Getu/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጽ/ቤት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ማሽቆልቆል እጅግ እንዳሳሰበው በዚሁ ሳምንት ይፋ አድርጓል ። «የፋኖ ደጋፊዎች» ናችሁ በሚል በርካታ የአማራ ወጣቶች መታሰራቸውን ያወሳው ተመድ የቤት ለቤት አሰሳ የጀመረው ቀደም ሲል መሆኑን ጠቅሷል ። የታሰሩ እንዲፈቱ፤ የመብት ጥሰት የፈጸሙ እንዲቀጡም ጠይቋል ።  አንድ ፉርኖ ዳቦ እስከ ዐሥር ብር፤ ደረቅ እንጀራ ከሃያ እስከ ሃያ አምስት ብር ደርሷል፤ በአጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ ንሯል ያሉ ነዋሪዎች በኑሮ ውድነቱ አማረዋል ። ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባልነቷ ከጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት እንደሚጀምር ይፋ መደረጉ ደግሞ ለሀገሪቱ ለውጥ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉ ተስፋ የሰነቁ አሉ። በዚያው ልክ ያጣጣሉም አሉ።

ተመድ ስለ ጅምላ እስሩና ሰብአዊ መብት ጥሰቱ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ይዞታ ማሽቆልቆሉ «እጅግ አሳስቦኛል» ያለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጽ/ቤት ይህንኑ በተመለከተ ማክሰኞ ዕለት መግለጫ ሰጥቷል ። የጽ/ቤቱ ቃል አቀባይ ማርታ ሑርታዶ ስዊትዘርላንድ፤ ጄኔቫ ከሚገኘው የድርጅቱ መሥሪያ ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፦ በአማራ ክልል ግጭት ቢያንስ 183 ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰው ጅምላ እስር እንዲቆም አሳስበዋል ። 

«በመላው ኢትዮጵያ ከ1000 በላይ ሰዎች» በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ «ስለመታሰራቸው መረጃዎች ደርሰውናል»ም ብለዋል ። የፋኖ ደጋፊዎች ናችሁ በሚል አብዛኞቹ የተያዙ ሰዎች የአማራ ብሔር ተወላጅ ወጣቶች ስለ መሆናቸው ተመድ መረጃ እንደደረሰውም ቃል አቀባዩዋ ተናግረዋል ። የመብት ጥሰት ፈጻሚዎች ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ሲል ተመድ ማሳሰቡንም ገልጸዋል ። ይህን ተመድ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታሰሩ ሲል በቃል አቀባይዋ በኩል ያሰማውን ንግግር በተመለከተ፦ «አሐዙ አንሷል በደንብ አልተዘገበም» ያሉት አበበ አዳምጤ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ። ኢትዮ ታይምስ በሚል የፌስቡክ ስም ደግሞ የቀረበ አጠር ያለ ጥያቄ፦ «1000 ሰው ብቻ ነው የታሠሩት? አይ ቀልድ» በሚል ይነበባል ። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጽ/ቤት ዓርማ በኒውዮርክ ከተማ ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጽ/ቤት ዓርማ በኒውዮርክ ከተማ ። የተመድ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጽ/ቤት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ማሽቆልቆል እጅግ እንዳሳሰበው በዚሁ ሳምንት ይፋ አድርጓል ።ምስል Carlo Allegri/REUTERS

አንተ ሰው አድነኝ የተባሉ ሌላ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ «የፋኖ ደጋፊ ብቻ አይደለም በአማራ ክልል የሚታሰራው ። ፀጉሩን ያሰደገ ወጣት ይታሰራል፤ ይገረፋል፤ አለበለዚያም ይገደላል» ብለዋል ። 

«አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ግጭት በጣም አደገኛ ነው መንግስት በአግባቡ ግምግሙ የፖለቲካ ማሻሻያ ማድረግ አለበት» ሲሉ ስጋታቸውን የገለጹት ደግሞ ማራማዊት የሰውዘር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ።

ተመድ ከነሐሴ መጀመሪያ አንስቶ የቤት ለቤት አሰሳ ይካሄድ እንደነበር፤ በአማራ ክልል ውስጥየሚሠሩ ሦስት ጋዜጠኞችም መታሰራቸውን ገልጿል። እንደ ተመድ ሁሉ የፈረንሳዩ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድንም (RSF) ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ውስጥ በዘፈቀደ እንደሚታሰሩ በትዊተር መልእክቱ ዘግቧል ። «በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል አማራ ክልል ውስጥ ያለውን ውጥረት የዘገቡ ቢያንስ 11 ጋዜጠኞች ተይዘዋል»ም ብሏል።  ጋዜጠኞቹን ጨምሮም፦ «ሀገሪቱ ውስጥ በዘፈቀደ የታሰሩ» ያላቸው «ሁሉም የመገናኛ አውታር ባለሞያዎች» እንዲፈቱ ሲልም ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ጥሪ አስተላልፏል። 

ያሻቀበው የኑሮ ውድነት

በኢትዮጵያ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ እጅግ ያሻቀበው የሸቀጦች ዋጋ የኑሮ ውድነቱን ማባባሱ እየተነገረለት ነው ። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተጠቃሚዎች ስለ ኑሮ ውድነቱ የተለያዩ ሸቀጦች ላይ የተጨመረውን የዋጋ ንረት በማነጻጸር አብራርተዋል ። ከአነስተኛ ፉርኖ ዳቦ እስከ አንድ ደረቅ እንጀራ፤ ከአንድ ኪሎ ጤፍ እስከ አንድ ሊትር ዘይት፤ ከሳሙና እስከ ትምህርት ቤት ወርኃዊ ክፍያ ወዘተረፈ ላይ ያለውን ከፍተኛ ጭማሪ በመጥቀስም ኑሮው እጅግ እንደከበዳቸው ገልጸዋል

 የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ ።
በኢትዮጵያ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ እጅግ ያሻቀበው የሸቀጦች ዋጋ የኑሮ ውድነቱን ካባባሰባቸው አካባቢዎች መካከል ዋና ከተማዪቱ አዲስ አበባ አንደኛዋ ናት ። የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ ።ምስል Seyoum Getu/DW

ምስጋናው ዮሐንስ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ፦ «መኖር በኢትዮጵያ ከባድ ሆነ» ብለዋል በአጭር መልእክታቸው ። ጋዳላ ገበሌ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪም በአጭሩ «መኖር ከብዶናል» ብለዋል ። «ኧረ ምኑ ይነገር ፈጣሪ ይህን ይፍታው» ይኼ ደግሞ የኮኪ ግርማ ዘለቀ መልእክት ነው ። 

«ምን ያደርጋል እያረሩ መሳቅ ሆኖብናል የአዲስ አበባ ኑሮ» ይላሉ እንዳለ ሹሜ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚ ። እስማኤል ጋሹ ደግሞ፦ «ዋናው ምክንያት የሰላም እጦት ነው» ይላሉ። «ሰላም ለሀገራችን» ሲሉም ይመኛሉ ። 

ሰሎሞን አሳምነው፦ ከሌሎቹ ዘለግ ያለ መልእክት አስፍረዋል። «በኑሮ ውድነቱ የተነሳ ከአዲስ አበባ ወደ ገጠሩ ለመሰደድ ፈልገን በመንገድ መዘጋት ለሌላ ቀውስና ለተደራራቢ ርሐብ ተጋልጠናል» በሚል ይንደረደራል ጽሑፋቸው ። «ቢያንስ መንገዱ ቢከፈት ሕይወታችን ማትረፍ እንችል ነበር » እያሉ ይቀጥላሉ። «አዲስ አበባ ውስጥ በማንነታችን ምክንያት ጅምላ እስሩ ተንቀሳቀሰን እንዳንሠራ አድርጎናል። በጣም ከምለው በላይ ነገሮች ከፍተዋል» ሲሉም ያጠቃልላሉ ።

ደስታ ተክሉ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ ትናንት ጭማሪ ተደርጎ የተሻሻለውን  የነዳጅ ዋጋ ተመን በማጣቀስ ጭማሪው ኅብረተሰቡን ለተጨማሪ የኑሮ ውድነት ያጋልጣል ብለዋል ። «ይህ ጭማሪ የምግብ ዋጋ እንዲንር ያደርጋል» በማለትም የነዳጅ እጥረቱን የሚቀርፍ አፋጣኝ ርምጃ ያሻል ብለዋል ። «ኑሮ ውድነት ብቻ አይደለም» ያሉት ደግሞ አበቃ ዘመኑ ናቸው በፌስቡክ ጽሑፋቸው ። «የደሀ ቤት መፍረስ፤ ጉቦ፤ ሌብነት፤ የመንግስት ሠራተኛች ሕዝብን ማንገላታት፤ ደሀ ፍትህ ማጣቱ፤ ሌላም ችግር የድሮው ደጉ ሕዝብ፤ አማኙ ሕዝብ ከእምነት የወጣ መሆኑን ተግባራችን ያሳያል» ብለዋል ። 

አበራ አደም የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «በኑሮ ውድነት ምክንያት አብዛኛው ኅብረተሰብ ክፍሎች ለረሃብ ተዳርጓል ። ከፍተኛ ችግር ነው ያለው ። ለአብነት ያህል፦ የት/ት ቤት ክፊያ እጅግ ጨምሯል ። ሰዎች ታመው መታከም አልቻሉም»  ሲሉ የኑሮ ውድነቱ ያሳደረውን ተጽእኖ አብራርተዋል ።

«ለማን ይነገራል?» ሲሉ ይጠይቃሉ ሳሚ ኪንግ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ።  «ለማንስ አቤት ይባላል?» ደግመው ያጠይቃሉ ።  «ሰሚ መንግስት ሲኖር አይደል እንዴ» ለራሳቸው ጥያቄ ራሳቸው መልስ በመስጠት ጽሑፋቸውን ይቋጫሉ ። 

የአትክልት ገበያ በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች ዳርቻ ።
በኢትዮጵያ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ እጅግ ያሻቀበው የሸቀጦች ዋጋ የኑሮ ውድነቱን ማባባሱ እየተነገረለት ነው ። የአትክልት ገበያ በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች ዳርቻ ። ምስል Seyoum Getu/DW

«ብልፅግና ይኑርልን እንጂ፤ ይሄው ኑሮ ውድነቱን አለማምዶን፣ በኑሮ ውድነት አበልፅጎን ምሳና እራታችን ጥብስ ሆንዋል » ጽሑፉ የዓሊ ሠይድ ነው ። በዚሁ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ስለመጋበዟ ወደሚያወሳው ዘገባችን እንሻገር ።

ኢትዮጵያ እና ብሪክስ 

ሩስያ እና ቻይናን ጨምሮ አምስት ሃገራት ያቋቋሙት የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር በእንግሊዥኛው (BRICS) ሰሞኑን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሃገራትን በአባልነት መቀበሉን ዐስታውቋል ። ከሦስት ወራት በኋላ በሚጠባው የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ ፣የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች፣ ግብፅ፣ እና አርጀንቲና ሙሉ ለሙሉ በአባልነት እንደሚቀጥሉም ተገልጿል ። 

የብሪክስ ዋነኛ ዓላማ፦ በዓለም ዙሪያ ፍትሐዊ አስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፍን ብሎም በምዕራባውያን በኩል ያለውን የኤኮኖሚ የበላይነት መቀልበስ መሆኑ ይነገርለታል ። የኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል ትሆናለች መባሉ እጅግ ያስፈነደቃቸው እንዳሉ ሁሉ ያጣጣሉም አሉ። 

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ ንግግር በሚያሰሙበት አጠር ያለ የማኅበራዊ መገናኛ የቪዲዮ መልእክት፦ «ኢትዮጵያ የመደመጥ አቅሟ እያደገ መምጣቱ» የብሪክስ አባል ከሆነችበት ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል ።  ደረጀ መላኩ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ «ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ ማኅበረሰብ መቀላቀሏ ለመጻዒው አምደ_ብዙ ፖለቲኮ_ኢኮኖሚያዊ፤ ሉላዊ ማለትም አጽናፋዊ እውነታ ተጠቃሚነቷን ያሳልጠዋል» ሲሉ ጽፈዋል ። ብርሃኑ አስማረ የተባሉ ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ ግን በጠቅላይ ሚንሥትሩ የቪዲዮ መልእክት ስር አንዲትም ቃል አላሰፈሩም ። ይልቁንስ በሳቅ የማንባት ምልክትን የሚያሳዩ የፊት ምስሎችን ደርድረዋል ። 

የብሪክስ ዓርማ በጆሐንስበርግ፤ ደቡብ አፍሪቃ ።
ሩስያ እና ቻይናን ጨምሮ አምስት ሃገራት ያቋቋሙት የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር በእንግሊዥኛው (BRICS) ሰሞኑን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሃገራትን በአባልነት መቀበሉን ዐስታውቋል ምስል Sergei Bobylev/TASS/dpa/picture alliance

ብሩክ ታደሰ በፌስ ቡክ መልእክታቸው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ስለመሆኗሲናገሩ፦ «ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምን አገኘች? ከአፍሪቃ ኅብረትስ?» ሲሉ ጠይቀዋል ።  «ከብሪክስም ምንም አታገኝም። "የድሀ ሀገር ቆንጆ" የምንም አባል ብትሆን ከማጨብጨብ የዘለለ ነገር እንዳትጠብቁ » ብለዋል ። 

ፍቅሩ በየነ፦ «ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗን ተከትሎ የሀገር ውስጥ የዜና ማሰራጫዎች ኢትዮጵያ በብልፅግና ዘመን በዓለም ላይ ተቀባይነት ማግኘቷን የሚያሳይ ነው እያሉን ነው» ሲሉ ጽሑፋቸውን ያንደረድራሉ ።

«የብሪክስ አባል አገሮችን ስንመለከት አብዛኛዎቹ በአሁኑ ጊዜ የዓለምን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የሚያንቀሳቅሱ ናቸው» ያሉት ፍቅሩ፦ «ኢትዮጵያን ከዛ አንፃር ካየን ከባድ ነው» ብለዋል ። የምእራባውያን ትኩረት ሊጨምር ይችላል፤ ከእነሱ ርዳታም ልታመልትጥ አትችልም ሲሉም ምክንያታቸውን ዘርዝረዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ