«ሀገራዊው ውይይት ከታቀደው ጊዜ ተገፍቶ ሊጀመር ይችላል»
ሐሙስ፣ ኅዳር 1 2015የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን የሚመራው ሀገራዊ ውይይት ከታቀደው ጊዜ ገፋ ተደርጎ ሊጀመር እንደሚችል ተገለፀ። ቀደምሲል ውይይቱ በመጪው ኅዳር ወር ይጀመራል ተብሎ ነበር።ሆኖም ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ዛሬ እንደተናገረው ውይይቱ እንዲጀመር ከመንግሥት ፣ ከሲቪክ ድርጅቶች እና ከሕዝብ ከፍተኛ ጫና" ቢኖርም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ቀላል ባለመሆናቸው ውይይቱ ከታቀደበት ጊዜ ይገፋል። ይህ የተባለው በኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መካከል የተደረሰ የትብብር ማዕቀፍ ዛሬ ሲፈረም ነው። ስምምነቱ ለአንድ አመት የሚዘልቅ ሲሆን ዴሞክራሲያዊ እና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ፣ የአካታችነት፣ እና የግልጸኝነት መርሆዎች ተጠብቀው ሰፊ ትምህርት እና ስልጠና ለሕዝብ እንዲሰጥ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ብሔራዊ ምክክሩ እንዲሳካ በጋራ ለመስራትን ያለመ ነውም ተብሏል።
የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተግዳሮትአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያቶችን ይለያል፣ ብቃት ባለውና በገለልተኛ አካል ውይይት እንዲካሄድባቸው ያደርጋል ፣ ቀጥሎ መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ይሰራል የተባለው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን እና ተጠሪነቱ ለእንደራሴው ምክር ቤት ሆኖ 4 ሺህ ያህል የሲቪል ድርጅቶችን የሚመራው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ለብሔራዊ ውይይቱ መሳካት ዛሬ ከተስማሙባቸው ጭብጦች ውስጥ "የዴሞክራሲያዊ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም የሕግ የበላይነት መርሆዎች መከበር፣ የአካታችነት ፣ ግልፀኝነት ፣ ቅቡልነትና አውድ አገናዛቢነት መርሆዎች የስምምነቱ አለባዊያን ናቸው። ውጤታማ እና እና ስኬታማ ሀገራዊ ምክክር የሚካሄድበት አስቻይ ሁኔታ መፍጠር፣ ስልጠና ፣ የመረጃ ልውውጥ ማመቻቸት" የሚሉት ይገኙበታል።የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ትኩረት ምን ሊሆን ይገባል? የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የሰሜን ኢትዮጵጵያን ጦርነት ለማስቆም የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሥራቸውን እንደሚያግዝና መሰል ስምምነቶች በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ይመጣሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ በዚሁ ወቅት ገልፀዋል።የኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ "ሁኔታው ዘላቂ እንዲሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያግዝ" ጠይቀዋል።ፕሮፌሰር መስፍን ውይይቱ በተጨባጭ መቼ ይጀመራል ሲል DW ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ።
"በስምንት ወር ውስጥ ብዙ መሠረታዊ ሥራዎችን ሰርተናል ብለን እናምናለን። ከእቅዳችን ትንሽ ዘግይተን ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን። ካለ የሰላም ጉጉት መነሻ ውይይቱ እንዲጀመር ከመንግሥት ፣ ከሲቪክ ድርጅቶች እና ከሕዝብ ከፍተኛ ጫና አለ። የዝግጅት ምእራፉን አገባደድን እና ጨረስን የምንለው ሕብረተሰቡን ለይተን ፣ አወያዮችን ለይተን ፣ ለአወያዮች ስልጠና ሰጥተን ፣ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ አስጨብጠን አጀንዳ ስንጨርስ ነው" ብለዋል። በሀገሪቱ ያሉ 1300 ወረዳዎችን በማጥናት ለውይይቱ ምቹ ሁኔታዎችን እየለዩ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በየቀበሌው ያለውን ሕዝብ ለማወያየት የመንግሥትን መዋቅር እንደማይጠቀሙ ገልፀዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ