1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ አለማግኘታቸው

ማክሰኞ፣ ኅዳር 18 2016

በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግር የተነሳ ተፈናቅለው አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ የተጠለሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ተናገሩ ። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ ተጠልለው ከሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 15 ህጻናት መታመማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4ZX1Y
ሆሮ ጉዱሩ ተፈናቃዮች በከፊል
ሆሮ ጉዱሩ ተፈናቃዮች በከፊል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

ከተፈናቃዮች 15 ህጻናት መታማቸው ተገልጿል

በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግር የተነሳ ተፈናቅለው አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ የተጠለሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ተናገሩ ። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ ተጠልለው ከሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 15 ህጻናት መታመማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል ። በመድኃኒት አቅርቦት እና ሰብአዊ ድጋፍ እጦት ለችግር መጋለጣቸውንነዋሪዎች ዐስታውቀዋል ። በአሙሩ ወረዳ ውስጥ ባለፈው ዓመት በነበረው የሰላም ችግር 10 ከሚደርሱ ቀበሌዎች ውስጥ ሰዎች ተፈናቅለው አጋምሳ የተባለ ከተማ ላይ ይገኛሉ ተብሏል ።

ከሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አስተዳደር እና አሙሩ ወረዳ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ።  የአሙሩ ወረዳ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት ወይም ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ወቅቱን ጠብቆ እየተሰጠ እንደሚገኝ ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር ። በኢትዮጵያየተፈናቃዮች ሁኔታ ትኩረት እንደሚያሻው በተደጋጋሚ ጊዜያት ይገለጻል ። 

በምግብ እጥረት የሕጻናት መታመም

በአሙሩ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ከ45ሺ በላይ ዜጎች እንደሚገኙ የወረዳው የአደጋ ስጋት አመራር ጽ/ቤት ወይም ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ በወረዳው ለሁለት ዓመታት ያህል በነበረው የሠላም እጦት ምክንያት ዜጎች ወደ ከተማ አካባቢ ተጠልለው እንደሚገኙም ተነግረዋል ። በአጋምሳ ከተማ ውስጥ ሚገኙት የተፈናቀሉ ዜጎች በተደጋጋሚ በቂ የሆነ ሰብአዊ ድጋፍ አለማግኘታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ  ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በምግብ እጦት ምክንያት ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን በአጋምሳ ከተማ የሚገኙ አንድ ነዋሪ  ጠቁመዋል ። በወረዳው ከዚህ ቀደም በሽፍቶች የሚደርሱ ጥቃቶች እና የቁም እንስሳት ዝርፍያ መቀነሱን የተናገሩት ነዋሪው በወረዳው ሰብአዊ ድጋፍ አነስተኛ መሆኑንና የመድኃኒት አቅርቦት በአካባቢው አለመኖሩን ገልጸዋል ።

በኦሮሚያ ክልልኪረሙ
በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግር የተነሳ ሰዎች ከሚፈናቀሉባቸው አካባቢዎች አንዷ ኪረሙ ናትምስል Privat

ለሦስት ዓመታት ያህል የግብርና ሥራ ተቋርጧል

በአጋምሳ ከተማ  ተጠልለው የሚገኙት ሌላው ነዋሪም በወረዳው ለሦስት ዓመታት ያህል የግብርና ሥራ በመቋረጡ በመንግሥት በኩል ከሚጠበቀበው ሰብአዊ ድጋፍ በስተቀር የግብርና ምርት አለመኖሩን ጠቁመዋል ። በወረዳው ከሚገኙት የተፈናቀሉ ዜጎች በተጨማሪም በቅርቡ በአሙሩ ወረዳ አዋሳኝ ከሆነው ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ሶንቶም ከሚባል ስፋራ በኅዳር ወር መጀመሪያ በነበረው ግጭት ወደ አራት ሺ ሰዎች ወደ አሙሩ ወረዳ መሻገራቸውን  ገልጸዋል ። ሰብአዊ ድጋፍ ከሦስት ቀን በፊት ከሶንቶም ቀበሌ ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ መሰጠጡቱን ነዋሪው ጠቁሟል ። «በአሙሩ ወረዳ በምግር፣ ጆጅ እና አጋምሳ ላይ ነው ተጠልለው የሚገኙት ። ብዙ ህጻናት እየታመሙ ነው ። ህክምና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ ባለመሆኑ መድኃኒት አጥተው  እየተቸገሩ ነው ። አጋምሳ ከተማ ላይ ከተጠለሉት በላይ ጆጅ በተባለ ቦታ ነው በርካታ ህጻናት የታመሙት ።» 

በአሙሩ ከ45ሺ በላይ ሰዎች በጊዜያዊ መጠለያ ኑሮን ይገፋሉ

በአሙሩ ወረዳ  ዜጎች መካከል 15 ህጻናት መታመማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል
በተለያዩ ጊዜያት ማንነት ላይ ባነጣጠሩ ጥቃቶች ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል በአሙሩ ወረዳ ዜጎች መካከል 15 ህጻናት መታመማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአሙሩ ወረዳ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ  ጅረኛ ረጋሳ ከዚህ ቀደም የተፈናቃዩችን ሁኔታ በተመለከተ በሰጡን ሀሳብ ሰብአዊ ድጋፍ ከተወሰኑ ቦታዎች ውጪ ወቅቱን ጠብቆ እንደሚመጣላቸው ተናግረው ነበር ። «የተፈናቀሉ ሰዎች ቅሬታ ሙሉ በሙሉ ተመልሷል ባይባልም ። ድጋፍ በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት እየመጣላቸው ነው ። በወረዳችን 45ሺ 500 ሰዎች ተፈናቅለው ይገኛሉ ። በመንግስትም ይሁን በግል ተቋማት በሚመጣበት ወቅት ለሁሉም እናከፋፍላለን ።»

ጥቅምት 30 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በአሙሩ ወረዳ አዋሳኝ  በሆነው ቡሬ ዙሪያ በቆ ጣቦና ሶንቶም በሚባሉ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በደረሰው ጥቃት 3149 ሰዎች ወደ አሙሩመፈናቀላቸውን ከወረዳው አስተዳደር የተገኘ መረጃ ያስረዳል ። ሶንቶም በተባለው ቀበሌ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ኅዳር 8 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በተከሰተው የታጣቂዎች ጥቃትም በሰዎች ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

መሳይ ተክሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ