የሱዳን ሰብአዊ ቀውስ መባባስ፤ ከጋና ምስጫ ምን እንማር?
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 12 2017የሱዳን ሰብአዊ ቀውስ መባባስ
በሱዳኑ የሽግግር ምክርቤት ፕረዚዳንት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና በባላንጣቸው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት አዛዣ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2023 ጦርነት ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ በሱዳን ከፍተኛ ነው የተባለለት ሰብአዊ ቀውስና የሰብአዊ መብት ረገጣ እየተከናወነ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱም ሃይሎች ወታደራዊ የበላይነትን ለመቀዳጀት ያስችሉኛል የሚሉአቸውን ቦታዎች ለመቆጣጠር በሚያደርጓቸው ፊልሚያዎች የበርካታ ስቪል ዜጎች ሕይወት እንደዋዛ ተቀጥፏል፤ በሺዎች የሚቆጠሩት ቆስለዋል ከ10 ሚልዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ተፈናቅለዋል አልያም አገር ጥለው ተሰደዋል።
በሁለቱም ሃይሎች መካከል ገበያዎችን ጨምሮ የስቪል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ኢላማ ያደረጉ የአየርን ጨምሮ የከባድ መሳሪያዎች ድብደባ በማካሄዳቸው ምክንያት የጉዳቱ መጠን ከፍ ሊያደርገው እንደቻለ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይገልጻሉ። ሁለቱም ጀነራሎች ግን በስቪል ዜጎች ለሚደርሱ ጥቃቶችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አንዱ ሌላኛውን በመክሰስ ለጉዳቱ ሃላፊነት መውሰድ እንዳልቻሉ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚስነር ቮልከር ቱርክ በሱዳን ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
« በአልፋሽር የሚታየው እመቃና ማለቂያ የሌለው ውግያ በየቀኑ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ነው። ይህ አሳሳቢ ሁኔታ መቀጠል የለበትም። የፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ይህን አስከፊ እመቃቸውን ማቆም አለባቸው። እንዲሁም በግጭቱ እየተሳተፉ ያሉ ሃይሎች ስቪሎችን እና የስቪል ተቋማትን ማጥቃታቸውን ማቆም አለባቸው። ሁለቱም ወገኖች ሊተገብሯቸው ቃል የገቡላቸውን ዓለምአቀፍ ውሎች፣ ዓለምአቀፍ ስምምነቶችና ህጎች እንዲያከብሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ። »
በምዕራባዊ የሱዳን ግዛት የምትገኘው የአልፋሻር ከተማ የሰብአዊ ቀውሱ ከተባባሰባቸው በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። የፈጥኖ ደራች ሃይሎች ሰራዊት ዙሪያዋን ከቦ በዕመቃ ሥር በማዋሉ በአካባቢው ለሚኖሩ ሱዳናውያን የሰብአዊ እርዳታና ሕክምና ተደራሽ ማድረግ እንዳልተቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከምንም በላይ ደግሞ ወደ ከተማዋና ወደ ስቪል ተቋማት የሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች በየዕለቱ የብዙዎችን ሕይወት መቅጠፋቸውን ቀጥለዋል።
« በሳምሳም የመጠለያ ጣቢያና በአልፋሽር ከተማ በስቪሎች ላይ የሚደርስ ጥቃት አስከፊ በሚባል ደረጃ እየተፈጸሙ ነው። በአካባቢው ያለው ረሃብን ጨምሩ አጠቃላይ የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ በጣም አስከፊ ነው። እነዚህን ጥቃቶችን ለመከላከልና እመቃው እንዲያበቃ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ጭምር ሁሉንም አይነት ጥረቶች ይደረጋሉ።»
ይሁን እና አላፋሽርን ጨምሮ በሱዳን ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እያኅቆለቆለ እንደሆነ ይነገራል። በዘምዘም የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ወደ 100,000 የሚጠጉ ተፈናቃዮችም የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በሰለለ ድምጻቸው «የረጂ ያለህ!» ቢሉም በአካባቢው አንዴ ጋም አንዴ ቀዝቀዝ በሚል ጦርነትና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ምክንያት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ዕርዳታ ሰራተኞች ወደ አካባቢው የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ይገልጻሉ።
ሂዩማን ራይትስዎች የተባለ ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድን የሱዳን ተመራማሪ የሆኑት ሞሐመድ ኦስማን በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርሳቸው ለማድረጉ የሁለቱም ጀነራሎች ተዋጊዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ። በተለይም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት አባላትን ደግሞ የበለጠ ተወቃሽ ያደርጋሉ። በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ዕለሞታቸውን የሚጠባበቁ ወገኖችን ለመታደግ ተብለው በውሱን መልኩም ቢሆን የገባውን የዕርዳታ እህል ይዘርፋሉ በማለት።
በየመጠለያው የሚገኙ ነዋሪዎችም የሁለቱም ጀነራሎች ተዋጊ ሰራዊቶች በሚያካሂዱአቸው ውግያዎችም ሆነ ተቆጣጥረው በያዟቸው አካባቢዎች ከሚፈጽሙአቸው የሰብአዊ መብት ረገጣዎች በተጨማሪ የዕርዳታ እህል እንዳይደርስና የደረሰውንም በመዝረፍ ሕይወታቸውን የበለጠ አደገኛ እንዳደረጉባቸው ይገልጻሉ።
በሱዳን እየተካሄዱ ባሉ ጦርነቶች ምክንያን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድንን ጨምሮ በርካታ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ሥራቸውን አቁመዋል። ተረጂዎች ባሉባቸው አካባቢዎችም ውግያዎች እየተካሄዱ በመሆኑ ሕክምናን ጨምሮ የሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ አልተቻለም። በመሆኑም በሱዳን ያለው የሰብአዊ ቀውስ አስከፊ በሚባል ደረጃ መድረሱን ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር የገለጹት። እሳቸው ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል ቢሉም አሁንም በሱዳን የሰብአዊ ቀውሱ ተባብሶ እንደቀጠለ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አፍሪቃውያን ከጋና ምርጫ ምን እንማራለን?
የተቃዋሚው መሪ ጆን ድራማን ማሃማ በቅርቡበጋና በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫማሸነፋቸው በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ክንውን ነው። የጋና ምርጫ ኮሚሽን እንዳረጋገጠው የ66 ዓመቱ የማሃማ ፓርቲብሔራዊ የዴሞክራቲክ ኮንግረስ የሐገሪቱን መራጭ ድምፅ 56 በመቶውን በማግኘት ነው ምርጫውን ማሸነፋቸውን የተነገረው።
ጋናውያን ለውጥን የመረጡበት ምክንያት
በጋና ለምርጫ ከተመዘገበው አጠቃላይ 18 ነጥብ 7 መራጭ ሕዝብ 10 ነጥብ 3 ሚልዮኑ ከ18 እስከ 35 ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም ፕረዚደንቱ ለማሸነፍ የረዳቸው የምርጫ ቅስቀሳቸው በወጣቶች ሕይወት ለውጥ ላይ ያተኮረ ስለነበረ እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ጋና በውጭ ዕዳ ጫናና በኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ክፉኛ የተጎዳች ሐገር ብትሆንም ማሃማ ቢመረጡ ሙስናን እንደሚታገሉና ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ቅድሚያ እንደሚሰጡ አብዝተው በመቀስቀሳቸው ከመራጩ ሕዝብ አብዛኛውን ቁጥር የያዘውን የወጣቶችን ትኩረትን መሳብ ችለዋል።
በጋና የተካሄደው ምርጫ ለተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራት እንደዴሞክራሲ ልኬት እንደሚታይ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።
በጎርጎሮሳውያኑ መጪው 2025 በአፍሪቃ የሚካሄዱ ምርጫዎች ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል። ይሐውም አብዛኛዎቹ በዚሁ ዓመት ምርጫ ያካሂዳሉ ተብለው የሚጠበቁ ሐገሮች መሪዎች አምባገነኖች በመሆናቸው ነው ተብሏል።
እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በያዝነው 2024 ምርጫ ያካሄዱ እንደሞሪሸስ፣ ቦትሰዋናና ሶማሊላንድ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አድርገዋል። መሪዎቹ ለየሃገሮቻቸው መራጮች መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን ቃል ገብተዋል።
ይሁንና እንደ ብሩንዲ፣ ካሜሮን፣ ጋቦን እና ማሊ ባሉ ሐገሮች ተቃዋሚ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎቻቸው የሚታሰሩባቸውና የሚሳደዱባቸው ሐገሮች እንደሆኑ ይነገራል። ይህም በምርጫውና ውጤቱ ላይ ከወዲሁ ጥያቄዎች እንዲነሱ እያደረገ ይገኛል።
ቢን ግርሃም ጆንስ የምርጫ ተንታኝ ናቸው። እሳቸው ለDW የእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት በሰጡት አስተያየት በተለይም በካሜሮንና ጋቦን ስለሚካሄደው ምርጫ ተከታዩን ብለዋል።
«በካሜሮን ከፍተኛ ፉክክር ይኖራል ብየ አስባለሁ። ሐገሪቱን ለረዣም ዓመታት የመሩት ፓዎል በያ ከስልጣናቸው የሚያሰናብት ምርጫ ይሁን አይሁን የሚወሰን ብርቱ ፉክክር የሚደረግበት ምርጫ ይሆናል። በጋቦን ደግሞ ወታደራዊ አመራሩ እውነተኛና ታማኝነት ያለው የምርጫ ሽግግር ያደርግ ይሁን የሚል የሚታይ ይሆናል።»
የምርጫ ተንታኞ ጆንስ በምርጫ አሸናፊ ለመሆን የመራጩን የልብ ትርታ ማግኘት ያስፈልጋል ይላሉ። ጋና ያካሄደችው ምርጫ በአፍሪካ የዴሞክራሲ እድገት ልኬትን ለመመርመር ጠቃሚ እንደሆነ ያጋ አፍሪካ የተባለውን መንግስታዊ ያለሆነ ምርጫን የሚከታተል ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ኢቶዶዶ ይገልጻሉ።
« ዲሞክራሲ እንዲያድግ ጋና የበኩሏን የዴሞክራሲ ልምምድ ሙከራ አድርጋለች። የሐገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ከግል ፍላጎት ማስቀደም ትልቅ ተግባር ነው። ተሸናፊው ዕጮ ዶክተር ባዉሚያ ሽንፈታቸውን በመቀበል ሁከትና ግርግር እንዲፈጠር ባለማድረጋቸው ስማቸውን በወርቅ ቀለም አጽፈዋል።»
የምርጫ ሂደቱ ግልጽና ተአማኒ በመሆኑ የተቃዋሚው ዕጩ ሽንፈትን አምኖ ለመቀበል አስችሏቸዋል ያሉትኢቶዶዶ ለሌሎች አገሮችም የምናሳስበው ይህንኑ ነው ሲሉም ጨምረዋል። የጋናን ምርጫና ውጤቱ በምሳሌነት የሚጠቀስና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን በማከል።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ሽዋዬ ለገሰ