1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሃላባ ዞን የተንሰራፋው ሙስና ህብረተሰቡን አማሯል

ሰኞ፣ ጥር 8 2015

በደቡብ ክልል ሀላባ ዞን ተንሰራፍቷል ያሉትን የሙስና ተግባር መንግሥት መርምሮ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ሲሉ የዞኑ ተወላጆች በሰላማዊ ሠልፍ ጠየቁ ፡፡ ከዞኑ እንደመጡ የሚናገሩት ሠልፈኞቹ ‹‹ አንዳንድ የዞኑ አመራሮች የከተማ ቦታ እየተቀራመቱ ፣ የመንግሥትና የቀበሌ ቤቶችን በራሳቸውና በዘመዶቻቸው ሥም እያዛወሩ ይገኛሉ ›› ብለዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4MFB2
Äthiopien Protest gegen Korruption in Halaba
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሃላባ ዞን ነዋሪዎች ሙስና አማሮናል አሉ

በሙስና የተማረሩት የሀላባ ዞን ነዋሪዎች   

በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የደቡብ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ፊት ለፊት የተሰባሰቡት ሰልፈኞች በመቶዎች ይቆጠራሉ ፡፡ ከሀላባ ዞን እንደመጡ የሚናገሩት ሰልፈኞቹ በዞኑ ባለሥልጣናት እየተፈጸመ ይገኛል ያሉትን የመንግሥትና የህዝብ ሀብት ምዝበራ በኮሚሽኑ እንዲመረመርላቸው የሚጠይቁ ባነሮችን ይዘው ታይተዋል፡፡ በተለይም በዞኑ አመራሮች ተገንብተዋል ያሏቸውን የመኖሪያ ቪላዎች በያዟቸው ፎቶ ግራፎች እና ባነሮች ላይ በማተም በሰልፋቸው ላይ አሳይተዋል ፡፡ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው ከሠልፉ አስተባባሪዎች ሁለቱ አቶ ብረሃኑ ሐሰን እና አቶ ራህማቶ ከድር ወደ ሀዋሳ የመጡት ለደቡብ ክልል መንግሥት እና ለክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ድምጻችንን ለማሰማት ነው ይላሉ ፡፡   

የመሬት ቅርጫ  

በሀዋሳ የተገኙት የሀላባ ዞን ቅሬታ አቅራቢዎች በዞኑ ተፈጽሟል ያሉትን ምዝበራ ያረጋግጡልናል  ያሏቸውን በርካታ ሰነዶች ለደቡብ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስገብተዋል፡፡ ለዶቼ ቬለ DW በቅጂ የደረሱት አብዛኞቹ ሰነዶች በመሬት ምዝበራ ላይ ያተኮሩ ናቸው ፡፡ ከሰነዶቹ መካከል የደቡብ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ከሀላባ ዞን ኮንስትራክሽን መምሪያ ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎችና የአጣሪ ኮሚቴ የምስክ ግምገማ ሪፖርት ይገኙባቸዋል ፡፡ በሠነዶቹ በዞኑ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ከሊዝ አዋጅና መመሪያ ውጪ በምደባ የተሰጡ መሬቶች ህጋዊነትን የተከተሉ ባለመሆናቸው ዞኑ አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቅበት ደብዳቤ ይጠቀሳል ፡፡ ከሀዋሳው ሠልፍ አስተባባሪዎች አንዱ አቶ ብረሃኑ ሐሰን ከሊዝ ጨረታ ውጪ በሺህዎች ካሬ ሜትር የሚቆጠረው መሬት አለአግባብ የተሰጠው ከህግ የግንዛቤ ማነስ የመነጨ አይደለም ይላሉ ፡፡ ይልቁንም የዞኑ አመራሮች ሁን ብለው የቅርብ ቤተሰቦቻቸውንና በዙሪያቸው የተሰባሰቡ ጥቂት ባለሀብቶችን ለመጥቀም በማሰብ መሆኑን ነው አቶ ብረሃኑ የሚናገሩት ፡፡ በደቡብ ምዕራብ ክልል የትምህርት ማስረጃን ያጭበረበሩ ላይ ርምጃ ተወሰደ

አውን የመኖሪያ ቤቶቹ እንደ ውሃ ተነኑ ?   

Äthiopien Protest gegen Korruption in Halaba
የሃላባ ዞን ነዋሪዎች በሐዋሳ ከተማ ያካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሀዋሳው ሠልፍ አስተባባሪዎች እንደሚሉት በሀላባ ዞን የሙስና ሲሳይ ከሆኑት መካከል የመንግሥትና የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ይጠቀሳሉ ፡፡ በዞኑ የሚገኙ የቀበሌ ቤቶች በራሳቸው አሊያም በቅርብ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ሥም በማዘዋወር ወደ ግል ንብረትነት እየተቀየሩ እንደሚገኙ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል ፡፡  ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀላባ ቂሊቶ ከተማ ብቻ 900 የሚደርሱ የመንግሥትና የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ መረጃው አለን የሚሉት የሠልፉ አስተባባሪዎች አቶ ራህማቶ ከድር እና አቶ ብረሃኑ ሐሰን ‹‹ አሁን በተጨባጭ በቁጥር ያሉት ቤቶች 300 አካባቢ  ብቻ ናቸው ፡፡ የቀሩት የት ገቡ ? ወይስ እንደ ውሃ ተነኑ ? ›› በማለት የሚጠይቁት አስተባባሪዎቹ የሚመለከተው አካል ሊያጣራና ሊመረምረው እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡ በሀሰተኛ ማስረጃና ቅጥር የፈተነው የደቡብ ክልል

የሀላባ ዞን መስተዳድር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ  

ዶቼ ቬለ DW በሰልፈኞቹ አቤቱታ ዙሪያ የሀላባ ዞን ዋና እና ምክትል አስተዳዳሪዎችን ለማነጋገር ቢጠየቅም ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑለትም ፡፡ የዶቼ ቬለ DW ዘጋቢ ሠልፈኞቹ አቤቱታ ወደ አቀረቡበት የደቡብ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበራ ኪጴ ቢሮ ቢያመራም ኮሚሽነሩ የፓርቲ ስብሰባ ላይ በመሆናቸውና ሥልክም ይዘው ሥለማይገቡ ሊያገኛቸው እንደማይችል ፀሐፊያቸው ገልጻለታለች ፡፡ ይሁን እንጂ በኮሚሽነሩ ወንበር ተወክለዋል የተባሉትን አቶ ታፈሰ ታደሰን ማነጋገር እንደሚችል በፀሐፊዋ ባገኘው ጥቆማ መሠረት አሁንም ሥለጉዳዩ አቶ ታፈሰን ጠይቋል ፡፡ ተወካዩ አቶ ታፈሰ ግን  ‹‹ አለቃዬ ሳይፈቅድ ( ኮሚሽነሩን ማለታቸው ነው ) መረጃ መስጠት እልችልም ›› በማለታቸው ለጊዜው የኮሚሽኑን አስተያየት በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም ፡፡ ያም ሆኖ ሠልፈኞቹ አሉን የሚሏቸውን ሠነዶች እና ማመልከቻዎች ለኮሚሽነሩ እንዲደርስላቸው በመዝገብ ቤት በኩል ማስገባታቸውን ዶቼ ቬለ DW ከሠልፉ አስተባባሪዎች አረጋግጧል፡፡  

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ