በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የበይነመረብ ተጠቃሚነት ያስከተለው ጫና
ረቡዕ፣ ጥቅምት 20 2017በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት ወይም በይነመረብ የሰዎችን የዕለት ተዕለት ህይወት የተቃና ለማድረግ እና ለሀገራት እድገት ወሳኝ ነው።ያም ሆኖ በቅርብ የወጡ ሁለት ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ የበይነመረብ ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ነው።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በኢትዮጵያ የበይነመረብ ተጠቃሚነት ችግር የሚያስከትለውን ጫና ይቃኛል።
ባለንበት የዲጅታል ቴክኖሎጅ ዓለም ኢንተርኔትወይም በይነመረብ በሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወትም ሆነ በሀገራት ሁለንተናዊ እድገት ላይ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።ኢትዮጵያም በጎርጎሪያኑ ሀምሌ 2020 ዓ/ም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን፣ የዜጎችን ተሳትፎ እና የተሻሻለ የህይወት ጥራትን ለማምጣት የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስትራተጂ ነድፋለች።ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የዲጅታል ክፍያ እና ግብይት እየጨመረ ሲሆን፤ በተለይ የመንግስት አገልግሎት ክፍያዎች ቴሌብር በሚባለው መተግበሪያ እንዲከናወን እየተደረገ ነው።
ዝቅተኛ የበይነመረብ ነጻነት
ይሁን እንጂ ለዲጂታል እድገት ቁልፍ የሆነው በይነመረብ አጠቃቀም በሀገሪቱ ውስጥ አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን የቅርቡ ጊዜ መረጃዎች ያሳያሉ።
ፍሪደም ሃውስ የተባለው የመብት ተሟጋች ተቋም ፤ የ2024 የኢንተርኔት ነፃነትን አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ ከ17 የአፍሪቃ ሀገራት መካከል ከመቶ የመመዘኛ ነጥቦች 27 በማግኝነት ዝቅተኛ የበይነመረብ ነፃነት ያላት ሀገር መሆኗን አመልክቷል።
ፍሪደም ሀውስ አያይዞም በአፍሪካ የኢንተርኔት ነጻነት እየተሻሻለ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ በግጭቶች እና በባለሥልጣናት እርምጃ ምክንያት በይነ መረብ ነጻ ያልሆነባት ሀገር መሆኗን ገልጿል። ዘገባው በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የሚያጋጥሟቸውን ጉልህ ተግዳሮቶች የዳሰሰ ሲሆን፤ እንደ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ባሉ ግጭት በተከሰተባቸው ሀገራት ያሉ መንግስታት የብሄራዊ ደህንነት ስጋትን እንደ ምክንያት በማድረግ የኢንተርኔት አገልግሎትን በተደጋጋሚ ያቋርጣሉ ብሏል።
76 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በይነመረብ አይጠቀምም
በሌላ በኩል ዓለምአቀፉየተንቀሳቃሽ ስልክ ግንኙነት ማህበር በእንግሊዝኛው ምህፃሩ /GSMA/ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ 76 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የበይነመረብ አገልግሎት ያለበት አካባቢ ቢሆን እንኳ በተንቀሳቃሽ ስልክ የበይነመረብ አገልግሎት አይጠቀምም።
ሀገር በቀሉ የመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል በምህፃሩ /CARD/ም ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ የበይነመረብ አጠቃቀም ችግሮች ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። የማዕከሉ የፕሮግራም ክፍል ሀላፊ አቶ መንግስቱ አሰፋ ከጥናቶቹ በመነሳት እንደገለሚገልጹት የኢንተርኔት ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ ዝቅተኛ ነው።
«የኢንተርኔት ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ ውስጥ ዝቅተኛ እንደሆነ ይታወቃል።የተለያዩ ሪፖርቶችም የእኛን ጥናት ጨምሮ ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት ማለት ነው።በዚህ ዘመን በዲጅታል ዓለም በሚባልበት ጊዜ ከኢንተርኔት የተለዬ ኑሮ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወይም ሀገራት ዘርፈ ብዙ የሆነ ጣና ውስጥ ነው የሚገቡት።ይህ ደግሞ «ኢምፓክት» ይኖረዋል በአጠቃላይ ማለት ነው።እነዚያን ኢምፓክቶች በተለያዩ ነገሮች ከፍለን ልናይ እንችላለን።» በማለት ገልፀዋል።
የበይነመረብ ተጠቃሚነት ዝቅተኛ መሆን ዘርፈብዙ ችግሮችን ያስከትላል
የበይነመረብ ተጠቃሚነት ዝቅተኛ መሆን ከሚያስከትላቸው ዘርፈብዙ ችግሮች መካከልም መረጃ የማግኘት መብትን መገደብ አንዱ መሆኑን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌን በመጥቀስ ያብራራሉ።
«በመጀመሪያ ደረጃ ከካርድ አንፃር ወይም ደግሞ ከመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል አስተሳሰብ አንፃር ስናየው መረጃን የማግኘት መብት ዓለማቀፋዊ የሆነ መሰረታዊ ከሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ውስጥ የሚገባ ነው።አንድ ሰው በየትኛውም ሁኔታ መረጃን ማግኘት አለበት። በተመሳሳይ ስዓት ሀሳቡን ያለምንም ገደብ በየትኛውም መገናኛ ዘዴ በይነመረብን ጨምሮ ማለት ነው ማስተላለፍ ሰብዓዊ የሆነ [ዓለማቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ} ውስጥም የተመጠ አንዱ መርሆ ነው።ከዚህ አንፃር የኢንተርኔት በተለያዩ ምክንያቶች መገደብ ወይም ዝቅተኛ የሆነ ተደራሽነት መኖር በዚያው ልክ የሰብዓዊ መብት ገደብ ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነገር ነው ማለት ነው።»በማለት አቶ መንግስቱ አብራርተዋል።
የበይነመረብ ተጠቃሚነት ለኢኮኖሚ እድገት
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የተንቀሳቃሽ ስልክ የበይነመረብ ተጠቃሚነት 10 በመቶ በጨመረ ቁጥር በአፍሪካ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት በነፍስ ወከፍ እስከ 2.5 በመቶ እንደሚጨምር ይገመታል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ጂ.ኤስ.ኤም ኤ ሰሞኑን ባዘጋጀው የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሪፖርት ላይ እንደጠቀሰውም የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ በጎርጎሪያኑ 2028 ማለትም ከ 4 አመታት በኃላ ኢትዮጵያ ከሚኖራት ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከ1.3 ትሪሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል። ከ 1 ሚሊዮን በላይ ደግሞ አዳዲስ ሥራዎችን ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት እየታዬ ያለው አነስተኛ የበይነመረብ ተጠቃሚነት መሻሻል ካላሳዬ በኢኮኖሚው የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም።አቶ መንግስቱ በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም በኢንተርኔት መቋረጥ በኢትዮጵያ የደረሰውን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ኪሳራ ያስታውሳሉ።
ዝቅተኛ የበይነመረብ አጠቃቀም የሚያስከትለው ኪሳራ
በኢትዮጵያ 90 ሚሊዮን የሚጠጋ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ እና ከ30 ሚሊዮን በላይ ደግሞ የበይነመረብ ተጠቃሚ መኖሩን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ያሳያል። ይህም ህብረተሰቡ ለአገልግሎቱ ያለውን ፍላጎት መጨመር ያሳያል። ይሁንና በሀገሪቱ በተደጋጋሚ በተለያዬ ወቅት እና አካባቢ ሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የሚጣሉ የበይነመረብ ገደቦች ፣የበይነመረብ ዋጋ ተመጣጣኝ አለመሆን፣ የዲጂታል ክህሎት ማነስ፣ የተደራሽነት ችግር ፣ተገቢነት እንዲሁም የደህንነት ስጋት ለበይነመረብ አጠቃቀም እንቅፋቶች መሆናቸውን የፍሪደም ሀውስም ሆነ የጂ ኤስ ኤም ኤ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ያሳያሉ።አቶ መንግስቱም የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል ባደረገው ጥናት ይህንኑ ችግር መመልከታቸውን ይገልፃሉ።
አካታች የበይነመረብ ተጠቃሚነት
በኢትዮጵያ የበይነመረብ ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር በከተማ እና በገጠር በሴቶች እና በወንዶች መካከልም ከፍተኛ የበይነ መረብ ተጠቃሚነት ልዩነት መኖሩንም GSMA የሀገራትን የ2024 የሞባይል ኢንተርኔት ግንኙነት በዳሰሰበት ዘገባው አመልክቷል። ይህንን መሰሉን ፍትሃዊ ያልሆነ የዲጅታል አጠቃቀም ለመቀነስም እንደ አቶ መንግስቱ አካታች የበይነመረብ ተጠቃሚነት እንዲኖር መስራት አስፈላጊ ነው።
«የገቢ ምንጫቸው የሚለያዩ ሰዎች ለምሳሌ «አፎርደብሊቲ» ብዙም ችግር ላይሆንባቸው ይችላል። ሌሎች ግን «አፎርድ» ላያደርጉ ይችላሉ።ስለዚህ በገቢ ደረጃ፣ በትምህርት ደረጃ፣በእድሜ፣ በፆታ፣እንዲሁም በከተማ እና በገጠር ነዋሪዎች መካከል ያሉ ኢ እኩልነቶችን ማለትም በሌሎች ዘርፎች ያሉ ልዩነቶችን ኢንተርኔትም የማባዛት አዝማሚያዎች አሉት።ያ እንዳይሆን አካታች የሆነ የኢንተርኔት ተደራሽነትን የምናረጋግጥባቸው ፖሊሲዎች፣ አሰራሮች እና ተቋማት መኖር አለባቸው።»ብለዋል።
የበይነመረብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ
በኢትዮጵያ የተንቀሳቃሽ የስማርት ስልኮችን ወደ ሀገር ለማስገባት 10% ቀረጥ እና 15% በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ ይጣላል። እነዚህ ወጪዎች ደግሞ 86 ሚሊዮን ህዝብ በድህነት ውስጥ ለሚኖርባት ሀገር ከአአቅም አንፃር ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል።በመሆኑም የተንቀሳቃሽ ስልክ የበይነመረብ ተጠቃሚነትን በሀገሪቱ ለማሳደግ በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ የሚደረግን ቀረጥ መቀነስ እና የማኅበረሰቡን ዲጅታል ክህሎቶች የሚያሻሽሉ መርሀ ግብሮችን መተግበር ጠቃሚ መሆኑን ተቋማቱ መክረዋል።አቶ መንግስቱ በበኩላቸው የበይነመረብ ዋጋን መቀነስ ፣ የበይነመረብ አስተዳደርን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ እንዲሁም የግለሰቦችን መረጃ መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር