1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ብሔራዊ ምክክር የኢትዮጵያን ቀዉስ ለማቃለል ይረዳ ይሆን?

እሑድ፣ ነሐሴ 28 2015

ኢትዮጵያም ዉስጥም ለረጅም ጊዜ መፍትሔ ያላገኙ፣ታሪካዊ፣ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ፣ ባሕላዊና አንዳዴም ኃይማኖታዊ ዉዝግቦችን ማስወገድ ባይቻል እንኳን ደም ማፋሳቸዉን ለማቃለል ብሔራዊ ድርድር እንዲደረግ በተለይ ከ1990ዎቹ (እግአ) ወዲሕ በተለያዩ ወገኖች ሲጠየቅና ሲሞከር ነበር

https://p.dw.com/p/4VrQ8
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አርማ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አርማምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ ቀዉስና ሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሚና

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ለዛሬዉ ዉይይታችን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ቀዉስ፣ የብሔራዊ ምክክር መፍትሔንና የምክክር ኮሚሽኑን ሥራና እቅዶችን ባጫጭሩ ለመቃኘት እንሞክራለን።እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1990 ጀምሮ ከደቡብ አፍሪቃ እስከ የመን ያሉ 17 ሐገራት የተለያየ መልክና ባሕሪ ያለዉ ብሔራዊ ምክክር ወይም ዉይይት አስተናግደዋል።ብሔራዊ ምክክር፣ እርቅ ወይስ ፍትህን ማስፈን ይቅደም 

 

ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ከ1991 እስከ 1992ና በ1993 የተደረገዉ ብሔራዊ ዉይይት ሒደቱና በጎ ዉጤቱ ሲደነቅ፣ እንደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሶማሊያ፣ አፍቃኒስታንና የመን ዉስጥ የተደረጉት ምክክሮች የየሐገራቱን ምስቅልቅል ችግሮች ለመፍታት ብዙ የተከሩት የለም ነዉ የሚባለዉ።የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስቸኳይ ሀገራዊ ጥሪ

የኢትዮጵያ ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽነሮችና የተወካዮች ምክር ቤት ኃላፊዎች
የኢትዮጵያ ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽነሮችና የተወካዮች ምክር ቤት ኃላፊዎች ምስል Solomon Muche/DW

ኢትዮጵያም ዉስጥም ለረጅም ጊዜ መፍትሔ ያላገኙ፣ታሪካዊ፣ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ፣ ባሕላዊና አንዳዴም ኃይማኖታዊ  ዉዝግቦችን ማስወገድ ባይቻል እንኳን ደም ማፋሳቸዉን ለማቃለል ብሔራዊ ድርድር እንዲደረግ በተለይ ከ1990ዎቹ (እግአ) ወዲሕ በተለያዩ ወገኖች ሲጠየቅና ሲሞከር ነበር።ጥያቄና ሙከራዉ በአብዛኛዉ ሥልጣን በያዙ ወገኖች እየተደፈለቀ፣ በተቀናቃኝ ወይም በተቃዋሚ ኃይላት ዳተኝነት እየተዘነጋ ወይም በአቅምና ትብብር ማጣት እየተዳፈነ ኢትዮጵያዉያን ሰበብና ምክንያቱን ለሚቀያየር ጦርነትና ግጭት ሚሊዮኖችን ለመገበር ተገድደዋል።

ተስፋና ሙግት የሚነሳበት ብሔራዊ ምክክር

«የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት» ሺዎችን በሚገድል፣ ሚሊዮኖችን በሚያፈናቅልበት መሐል ታሕሳስ ማብቂያ 2014 (እኢአ) «የኢትዮጵያ ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን» ተመሥርቷል።የኮሚሽኑ መመሥረት የከፋዉን ደም መፋሰስና ሥር የሰደደዉን ጠብና ልዩነት በዉይይትና በድርድር ለማርገብ ይረዳል የሚል ተስፋ መፈንጠቁ አልቀረም።

ኮሚሽኑ ለመንግስት የሚያዳላ ወይም «ከመንግስት ተፅዕኖ ያልተላቀቀ ነዉ» የሚል ወቀሳና ትችት ባይለየዉም ልዩነትን በድርድር የመፍታት ፅንሰ ሐሳብን በሕብረተሰቡ ዘንድ ለማስረፅ መጣሩ አልቀረም።ወጣቶችን በሀገራዊ ውይይቱ ለማሳተፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ

ለረጅም ጊዜ ሲጓተት የቆየዉን ብሔራዊ ምክክር በመጪዉ ጥር ለመጀመርም ቀን ቆርጧል።ኢትዮጵያ ግን የፖለቲካ ሥልጣን፣ የጎሳ፣ የግዛት ይገባኛል፣ የአስተዳደር አልፎ ተርፎ የባሕልና የኃይማኖት ልዩነት በሚጭረዉ ጦርነት፣ ግጭትና ጥቃት ከመዉደም አልተላቀቀችም።የሰሜኑ ጦርነት በዉጪ ኃይላት ጫናና ሽምግልና ቢቆምም ዛሬም አብዛኞቹ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ሕዝብ በመንግስትና በአማፂያን ግጭት፣ በዘር ላይ ባነጣጠረ ጥቃትና ማፈናቃል እያለቀና እየተሰቃየ ነዉ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ፅሕፈት ቤት-አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ፅሕፈት ቤት-አዲስ አበባምስል Solomon Muchie/DW

የሌላዉ አካባቢ ነዋሪም በዘረፋዎች፣ በአጋቾችና ወርሮበሎች እየተዋከበ፣ ወጥቶ ለመግባት፣ ሰርቶ ለመብላት እያዳገተዉ ነዉ።የኢትዮጵያ ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት ባለፈዉ ነሐሴ 2 ባወጣዉ መግለጫ «የሚመለከታቸዉ አካላት በሙሉ ልዩነታቸዉን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በምክክር እንዲፈቱ» ጥሪ ቀርቧል።ኮሚሽኑ «ባለድርሻ» ያላቸዉን አካላት ለማቀራረብና ለማወያየት አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር  ዝግጁ» ነኝ ብሏልም።ከኬንያ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያ ምን ትማር?

የኢትዮጵያን ምስቅልቅ፣ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ሥራና ለጥር የተቀጠረዉን ጉባኤ እንዴትነት ባጫጭሩ እንቃኛል።

ነጋሽ መሐመድ