1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተሻሻለው የጀርመን የዜግነት አሰጣጥ ሕግ

ማክሰኞ፣ ጥር 28 2016

በአዲሱ ሕግ ግን የጀርመን ዜግነት ለማግኘት የውጭ ዜጎች የጀርመን ቆይታ ከስምንት ዓመት ወደ 5 ዓመት ዝቅ ብሏል።ጥምር ዜግነትንም ይፈቅዳል።የመኖሪያ ፈቃድ ካለውና አምስት ዓመት ጀርመን ከኖረ የውጭ ዜጋ የተወለደ ህጻን ወዲያውኑ የጀርመን ዜግነት ማግኘት ይችላል። በፍጥነት ከኅብረተሰቡ ጋር የተዋሀዱ የውጭ ዜጎች በ3 ዓመት ዜጋ መሆን ይችላሉ።

https://p.dw.com/p/4c6pE
የጀርመን ዜግነት ያገኘት ወጣት ከጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጋር
የጀርመን ዜግነት ያገኘት ወጣት ከጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጋርምስል John Macdougall/ADP/dpa/picture alliance

የተሻሻለው የጀርመን የዜግነት አሰጣጥ ሕግ

የጀርመን የሕግ መምሪያና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች በማገባደድ ላይ ባለነው በጥር ወር ያጸደቁት የተሻሻለው የጀርመን የዜግነት አሰጣጥ ሕግ በጀርመን ጥምር መንግሥት አባላት የሶሻል ዴሞክራቶች፣ የአረንጓዴዎቹ  የነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲዎች በጎርጎሮሳዊው 2021 መጨረሻ ላይ ስልጣን ሲይዙ ተግባራዊ ለማድረግ ከተስማሙባቸው የማኅበራዊ ጉዳዮች ማሻሻያዎች አንዱ ነው። የተሻሻለው ሕግ ጀርመን የሚኖሩ የውጭ ዜጎች የጀርመን ዜግነት የሚያገኙበትን መንገድ የሚያቀልና ሂደቱንም የሚያፋጥን ተብሏል። ከዚህ ቀደም የውጭ ዜጎች የጀርመን ዜግነት ለማግኘት ስምንት ዓመት ጀርመን መኖር ይጠበቅባቸው ነበር።የጀርመን የዜግነት ሕግ ማሻሻያና ተግዳሮቱ በአዲሱ ሕግ ግን የጀርመን ዜግነት ለማግኘት የውጭ ዜጎች የጀርመን ቆይታ እንዲያጥር ተደርጓል። ከእስካሁኑ ስምንት ዓመት ወደ 5 ዓመት ዝቅ ብሏል። ይህ ከዚህ ቀደም የጀርመን ዜግነት ለማግኘት ከሚያስፈልጉት መስፈርቶች መካከል የተሻሻለው አንዱ መመዘኛ ነው።

የጀርመን ፕሬዝዳንትና ባለቤታቸው በተገኙበት የጀርመን ዜግነት አሰጣጥ ስነ ስርዓት በቤልቭዩ ቤተ መንግሥት
የጀርመን ፕሬዝዳንትና ባለቤታቸው በተገኙበት የጀርመን ዜግነት አሰጣጥ ስነ ስርዓት በቤልቭዩ ቤተ መንግሥት ምስል John Macdougall/ADP/dpa/picture alliance

ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋ እንደተናገሩት በተሻሻለው ሕግ በትምሕርት ቤት ፣በስራ ቦታ ወይም በተለያዩ የሲቪክ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በፍጥነት  ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋህደው መኖር የቻሉ የውጭ ዜጎች የጀርመን ዜጋ ለመሆን አምስት ዓመት መጠበቅ የለባቸውም። በ3 ዓመት ውስጥ ዜጋ የመሆን እድልም አላቸው። ይህ ግን በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙ ክርክር ያነሱበት ጉዳይ ነበር።ከዚሁ ጋር ግን የጀርመን ዜግነት ለማግኘት መሟላት ያለባቸው ሌሎች መስፈርቶችም አሉ። የጀርመን ዜግነት ያገኙ የውጭ ዜጎች
ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ካለውና አምስት ዓመት ጀርመን ከኖረ የውጭ ዜጋ የተወለደ ህጻን በአዲሱ ሕጉ መሠረት ወዲያውኑ የጀርመን ዜግነት ማግኘት እንደሚችልም ተጠቁሟል።
አዲሱ ሕግ ከቀድሞው የሚለየው ጥምር ዜግነትን መፍቀዱ ነው።ይህም ማለት የውጭ ዜጎች የየትውልድ ሀገራቸውን ዜግነት ይዘው የጀርመን ዜጋ መሆን የሚችሉበትን እድልም ይሰጣል።

በቀደመው ሕግ በተለየ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ለሁሉም የውጭ ዜጎች ይህ የሚቻል አልነበረም ከአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራትና ከስዊዘርላንድ ውጭ የሆነ ዜግነት ያላቸው የጀርመን ነዋሪዎች የጀርመን ዜግነት ለማግኘት መጀመሪያ የያዙትን ፓስፖርት የማስረከብ ግዴታ ነበረባቸው።

ጥምር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢራናዊ
ጥምር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢራናዊምስል Sven Simon/imago images

በአዲሱ ሕግ ግን ያ ተቀይሮ የነበራቸውን ፓስፖርትም ይዘው የጀርመን ዜግነት ማግኘት ይችላሉ። ይሁንና ይህ ማሻሻያ አሁንም ለሁሉም ሀገር ዜጎች ይሰራል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለየ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር የዚህ እድል ተጠቃሚ መሆን እንደማይችሉ ነው ዶክተር ለማ የገለጹት። የዚህ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጥምር ዜግነትን ባለመፍቀዱ ነው።
ከጀርመን ህዝብ 14 በመቶው ወይም ከ12 ሚሊዮን የሚበልጠው የጀርመን ዜግነት የለውም። የጀርመን የጥንድ ዜግነት ደንብከመካከላቸው ወደ 5.3 ሚሊዮኑ ቢያንስ ለአስር ዓመታት ጀርመን የኖሩ ናቸው። የእስከዛሬው የጀርመን ዜግነት አሰጣጥ ከሌሎች የአውሮጳ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓም የጀርመን ዜግነት ያገኙ የውጭ ዜጎች ቁጥር 168 ሺህ 500 ነበር። ይህ ከ2002 ዓም ወዲህ እጅግ ከፍተኛ የተባለ ቁጥር ነው። ጀርመን ዘንድሮ የዜግነት አሰጣጥ ህጓን በማሻሻሏ ብዙ ታተርፋለች። ጀርመን እንደ ፈረንሳይ ያሉ ጎረቤት የአውሮጳ ሀገራት ዩናይትድ ስቴትስና ካናዳን እንደ መሳሰሉ ምዕራባውያን ሀገራት የሰለጠነ የሰው ኃይል በቀላሉ ለመሳብ ያጸደቀችው የተሻሻለው የዜግነት ሕግ ዶክተር ለማ እንደተናገሩት በጥቂት ወራት ውስጥ ስራ ላይ ሊውል ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ