1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ጥሪ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 1 2015

35 አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች፤ አጥፊዎች የሚዳኙበት ገለልተኛ ምርመራና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ዛሬ ጠየቁ ። «የታመቁ ቅራኔዎች ወደ ነውጥ እንዳይሸጋገሩ ለመከላከል፣ ነውጥ አዘል ግጭቶች በሰላማዊ ንግግሮች እንዲፈቱ እና የሰላም ጅምሮች ሁሉን አካታች እና ዘላቂ እንዲሆኑ» በማለት ጠይቀዋል ።

https://p.dw.com/p/4W11J
35 የሲቪክ ማኅበራት የሰላም ጥሪ አስተላልፈዋል ።
35 የሲቪክ ማኅበራት «የታመቁ ቅራኔዎች ወደ ነውጥ እንዳይሸጋገሩ ለመከላከል፣ ነውጥ አዘል ግጭቶች በሰላማዊ ንግግሮች እንዲፈቱ እና የሰላም ጅምሮች ሁሉን አካታች እና ዘላቂ እንዲሆኑ» በማለት ጠይቀዋል ። ምስል Solomon/DW

ድርጅቶቹ የሰላም ጥሪያቸውን አስተጋብተዋል

የሲቪክ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ

35 አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዛሬ ባወጡት «የኢዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ» አገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች እና አጥፊዎች የሚዳኙበት ገለልተኛ ምርመራ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠየቁ ። እየተገባደደ ያለው 2015 ዓ.ም በአንድ በኩል የሰላም ጅምር ተስፋ ይዞ ቢመጣም በሌላ ጎኑ ግጭቶች ተባብሰው በዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ የሰላም እጦቱ ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሄድ ሥጋታቸው መሆኑንም ድርጅቶቹ ገልፀዋል ። የሲቪክ ድርጅቶቹግጭቶችን የሚፈታ ፍኖተ ካርታ እንደሚያስፈልግ የጠየቁ ሲሆን ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት እንዳትወጣ ያደረጉ እና ለሰላም መታጣት ብሎም ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት የሆኑ ያሏቸው ዐሥር መሠረታዊ ክፍተቶች ላይ የሰላም ጥሪ አስተላልፈዋል ። የሰላም ጥሪ አቅራቢ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች  «የታመቁ ቅራኔዎች ወደ ነውጥ እንዳይሸጋገሩ ለመከላከል፣ ነውጥ አዘል ግጭቶች በሰላማዊ ንግግሮች እንዲፈቱ እና የሰላም ጅምሮች ሁሉን አካታች እና ዘላቂ እንዲሆኑ» በማለት ጠይቀዋል ። ለዚህ መሳካት አጋዥ ሆነው እንደሚንቀሳቀሱም ባደረጉት ጥሪ ቃል ገብተዋል ።

2015 . እና አስከፊ ገጽታው እና የሰላም ጥረቶች

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ የታገዙ መፍትኄ ያላገኙ ግጭቶች ፣ አለመረጋጋቶች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች ፣ ከመዋቅር ጥያቄዎች ጋር የተገናኙ የሕዝብ ቅራኔዎች እና ተቃውሞዎች ፣ ማፈናቀሎች ፣ በዜጎች ላይ የተጣሉ የመንቀሳቀስ መብት ገደቦች ፣ የጅምላ እና የዘፈቀደ እሥሮች፣ አስገድዶ የመሰወር ድርጊቶች ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግድያ እና የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያጠቡ ያሏቸው ሁኔታዎች የሳምንት እድሜ በቀረው 2015 ዓ.ም የተስተዋሉ ጉልህ የኢትዮጵያ አስከፊ ገጽታዎች መሆናቸውን የሰላም ጥሪ አቅራቢዎቹ የሲቪክ ድርጅቶች ዘርዝረዋል።

እነዚህ የሲቪክ ድርጅቶች መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት እንዲቆም ተጀምሮ የነበረው የዛንዚባር ድርድር፣ በቤኑሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ተደረጉ ያሏቸው ስምምነቶች ተስፋ ሰጪ እንደነበሩም በበጎ ዘርዝረዋል።
የሰላም ጥሪውን ካቀረቡት ተቋማት መካከል የስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊ መሠረት ዐሊ በዓመቱ ደረሰ የተባለውን ጉዳት ዘርዝረዋል።

"ከ ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ. ም እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ. ም ውስጥ የፖለቲካ ግጭቶች እና ሁነቶች ብዛት 1073 ነው። በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ወደ 4027 አካባቢ ነበር። በሰላማዊ ሰዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር 1918 ደርሷል" ብለዋል።

35 አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ አስተላልፈዋል ።
35 አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዛሬ ባወጡት «የኢዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ» አገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች እና አጥፊዎች የሚዳኙበት ገለልተኛ ምርመራ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠየቁ ።ምስል Solomon/DW

የሰላም ጥሪው ዐቢይ ጉዳዮች ምንድን ናቸው ?

ዐሥር ነጥቦችን የያዘው የሲቪል ድርጅቶቹ "የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ" ውጥረቶችን በፖለቲካ ንግግር እና ምክክር ሳይሆን በኃይል የመፍታት የቆየ ያሉት ባህል በመኖሩ ይህ እንዲወገድ አገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች ይጠይቃል። ለተጎጂዎች ፍትሕ የሚሰጥ እና "ከበቀል አዙሪት" የሚያወጣ ብሎም ለፍትሕ ተቋማት ተዓማኒነት ይረዳል ያሉት ገለልተኛ ምርመራ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍንም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል ያሉት የፆታ ጥቃት ተገቢው ትኩረት እንዲያገኝ ፣ የተጋላጭ እና ግፉዓን ጥበቃ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ፣ በብዙኃን ይሁንታ የማያገኙ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ውሳኔዎች ከመተላለፋቸው በፊት ሕዝባዊ ተሳትፎን እንዲያረጋግጡ እና የቅድመ ግጭት መጠቆሚያ እና መከላከያ ሥርዓት እንዲኖር በሰላም ጥሪው ተካቷል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ የስብስቡን ጥሪ አቅርበዋል።"ዘንድሮም እልባት ያልተገኘላቸው ግጭቶች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ያሉ ሲሆን በዚህ ዓመት የተስተዋሉ አዳዲስ እና ነባር ግጭቶች በመጪው ዓመትም ተባብሰው እንዳይቀጥሉ ያሰጋል"

ኢትዮጵያለግጭት አዙሪት የዳረጋት ምንድን ነው ?

35ቱ ሀገር በቀል የሲቪል ድርጅቶቹ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ፣ የጥላቻ ንግግር እና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭቶች እንዲቆሙ ፣ የሲቪክ ምኅዳሩም ጥበቃ እንዲደረግለት ጭምር ጠይቀዋል።

ድርጅቶቹ በሚያቀርቡት ጥሪ ልክ ምላሽ እያገኙ እንዳልሆነ እና ይህም እንደሚያሳስባቸው፣ ፍትሕ እና ተጠያቂነት የምን ጊዜም ጥያቄዎቻቸው መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በቅርቡ በአማራ ክልል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅተከትሎ የተዋቀረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሥራውን ለመፈተሽ  እና ለማየትም እድል ማግኘት እንዳልቻሉም ድርጅቶቹ ገልፀዋል።

ዛሬ ጥሪ ያቀረቡባቸው አሥሩ ነጥቦች ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰላም መታጣት እና ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መበራከት የሆኑ ክፍተቶች ናቸው በማለት ግልጽ አድርገዋል። በዚህ ምክንያትም ሀገሪቱ ከግጭት አዙሪት ውስጥ መውጣት እንዳልቻለች እና አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲደርሱ አድርገዋል ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ