1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ከቻይና አበዳሪዎቿ “የዕዳ ጫና ለመቀነስ” እንድትደራደር መወሰኑን አሕመድ ሽዴ ተናገሩ

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 7 2016

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ሀገሪቱ “ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ” ከቻይና የፋይናንስ ተቋማት እንዲደራደር መወሰኑን አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ካለባት 28 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዕዳ 14 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና የተበደረችው ነው። መንግሥት ለሁለተኛው ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ከአይኤምኤፍ ባለሙያዎች የሚያደርገው ውይይት ተራዝሟል

https://p.dw.com/p/4XigI
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ሀገሪቱ “ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ” ከቻይና የፋይናንስ ተቋማት እንዲደራደር ውሳኔ መተላለፉን አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ የምታደርገው ውይይት ሲራዘም ከቻይና አበዳሪዎቿ “የዕዳ ጫና ለመቀነስ” ልደራደር ነው

በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ የጀመረችው ድርድር እጅግ የዘገየባት ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ቻይና አዙራለች። በቻይና የመቀነት እና መንገድ ዕቅድ ስብሰባ (Belt and Road Forum) ለመሳተፍ ቤጂንግ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 6 ቀን 2016 ከፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ ጋር ባደረጉት ውይይት ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ ይኸው የዕዳ አከፋፈል እንደሚገኝበት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ በተላለፈ ንግግራቸው ጠቁመዋል።

“ከአጭር ጊዜ አንጻር ኢትዮጵያ ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ ውሳኔ ወስነው የሚመለከታቸው የቻይና የፋይናንስ ተቋማት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ድርድሩን እንዲጨርሱ መመሪያ” መሰጠቱን የተናገሩት አቶ አሕመድ በዕዳ እፎይታ እና የዕዳ ሽግሽግ ረገድ “ትልቅ ውጤት” መገኘቱን ገልጸዋል።

የቻይና የወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ፣ የቻይና ልማት ባንክ፣ የቻይና ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ እና የቻይና የኢንዱስትሪ እና የንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ አበዳሪዎቿ መካከል ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ካለባት ዕዳ 14.1 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና የተበደረችው እንደሆነ የአሜሪካው ቦስተን ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀረው መረጃ ያሳያል። ባለፈው ነሐሴ በደቡብ አፍሪካ በተካሔደው ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በተረጋገጠበት የመሪዎች ጉባኤ ቻይና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለአንድ ዓመት የዕዳ ክፍያ እፎይታ ሰጥታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቻይና የመቀነት እና መንገድ ዕቅድ ስብሰባ (Belt and Road Forum) ለመሳተፍ ቤጂንግ ሲደርሱ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 6 ቀን 2016 ከፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ ጋር ከተወያዩ በኋላ “ኢትዮጵያ ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ ውሳኔ ወስነው የሚመለከታቸው የቻይና የፋይናንስ ተቋማት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ድርድሩን እንዲጨርሱ መመሪያ” መሰጠቱን አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ምስል Ken Ishii/REUTERS

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “መጠነ ሰፊ-የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ከቻይና የተገኘ እንደሆነ ምን አልባት ሌሎች አበዳሪዎችም ያንን ተከትለው” ተመሣሣይ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ፊቱን ወደ ቻይና ያዞረው በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል ከአበዳሪዎች ጋር የሚደረገው ድርድር እጅግ በተጓተተበት ወቅት ነው።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር አናሊሳ ፌዴሊኖ ከቻይና የአንድ ዓመት የዕዳ ክፍያ እፎይታ ያገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሌሎች አበዳሪዎቹ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚፈልግ ተናግረዋል። በአጠቃላይ 28.2 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረበው በሐምሌ 2013 ነው።

ኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር የዕዳ አከፋፈል ማስተካከያ ዕቅድ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ አበበ አዕምሮ ሥላሴ ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ እንዲደረግላት ጥያቄ የምታቀርበው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በጠየቀው ብድር ላይ ከተቋማቸው ባለሙያዎች ጋር ሥምምነት ላይ ሲደረስ እንደሆነ ተናግረዋል። ባለፈው ሣምንት በሞሮኮዋ ማራካሽ ከተማ በተካሔደው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ጥምር ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የአፍሪካ አገራትን የምጣኔ ሐብት ዕድገት ትንበያ በተመለከተ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ስለጉዳዩ የተጠየቁት አበበ የሚያስፈልገው ሥምምነት አለመኖሩን ገልጸዋል።

አበበ አዕምሮ ሥላሴ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ
ኢትዮጵያ ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ በጠየቀችው ድጋፍ ላይ ከተቋሙ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ቢደረግም ሥምምነት ላይ አለመደረሱን የአይኤምኤፍ የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ አበበ አዕምሮ ሥላሴ ተናግረዋል። በመስከረም ወደ አዲስ አበባ አቅንተው በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የተወያዩት ባለሙያዎች ከሥምምነት ሳይደርሱ ተመልሰዋል። ምስል picture-alliance/dpa

“ሀገሮች ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባልደረቦች ጋር ሥምምነት ላይ ሲደርሱ [የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ እንዲደረግ] ለጋራ ማዕቀፉ ያመለክታሉ። እስካሁን ሥምምነቱ የለንም” ያሉት አበበ የኢትዮጵያ “መንግሥት አሁንም በኤኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ላይ እየሰራ እንደሆነ አስባለሁ። ስለዚህ [በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች መካከል] የተደረሰ ሥምምነት የለም። [ሁለቱ ወገኖች] ሥምምነት ላይ ሲደርሱ ሒደቱ በቅንነት የሚራመድ ይመስለኛል” ሲሉ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 2 ቢሊዮን ዶላር ጠይቃለች። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከሰኔ 2013 ጀምሮ ተከታታይ ውይይቶች ሲያደርጉ ቢቆዩም እንደ ዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ድርድሩ ሁሉ ጉዳዩ ፈቅ ማለት ተስኖት ቆይቷል። ወደ አዲስ አበባ ያቀኑ የድርጅቱ ባለሙያዎች ከመስከረም 14 እስከ 22 ቀን 2016 የኢትዮጵያ መንግሥት ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ በጠየቀው ድጋፍ ላይ ውይይት ሲያደርጉ ቢቆዩም ያለ ሥምምነት ተመልሰዋል።

ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ የነበረውን የባለሙያዎች ቡድን የመሩት አልቫሮ ፒሪስ የጉብኝቱን መጠናቀቅ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ልዑካን “የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እና ኤኮኖሚውን ለማረጋጋት የተወሰዱ ጠቃሚ እርምጃዎች” መታዘባቸውን ገልጸዋል። እነዚህ እርምጃዎች ፒሪስ እንዳሉት “የፊስካል እና የገንዘብ ቁጥጥርን በከፍተኛ ደረጃ ማጥበቅን” የሚጨምሩ ናቸው። ፒሪስ በመግለጫቸው ባለሙያዎቹ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በጠየቁት ድጋፍ ላይ ያደረጉት ውይይት “በጎ እምርታ” ማሳየቱን ቢጠቅሱም የመጨረሻውን ውሳኔ ለሚያስተላልፈው የዓለም የገንዘብ ድርጅት ቦርድ የሚቀርብ ሥምምነት ግን አልተፈጸመም።

አዲስ አበባ ሜክሲኮ ዋሸበሌ አካባቢ የሕብረት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ከሩቅ
ኢትዮጵያ ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 2 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር በውይይት ላይ ትገኛለች። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሰራው የዕዳ ትንተና ኢትዮጵያ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2026 ባሉት ዓመታት 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ምስል Eshete Bekele/DW

ፒሪስ “ለተጠየቀው ፕሮግራም በሚያስፈልጉ ማሻሻያዎች ላይ በመጪዎቹ ሣምንታት ውይይቶች ይቀጥላሉ” ብለዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን በሁለቱ ወገኖች ውይይት “ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በገበያ እንድትተምን የሚያደርግ ቅድመ-ሁኔታ መግባቱ የማይቀር ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን በ55 ብር ገደማ የሚመነዘረውን ዶላር በተለምዶ “ጥቁር” እየተባለ ከሚጠራው የጎንዮሽ ግብይት ለማስተካከል ወደ 110 ከፍ ብር ያደርገዋል ብሎ ማሰብ “በጣም የሚከብድ ነው” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “ብዙ ጣጣ” ሊያስከትል ይችላል በሚሉት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ማሻሻያ ጉዳይ ሁለቱ ወገኖች መስማማት እንደሚቸገሩ ያምናሉ።

ይኸ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መካከል አለመግባባት ሊፈጥር የሚችል የውጭ ምንዛሪ ግብይት ጉዳይ በመጀመሪያው የሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ  መርሐ-ግብር ውስጥ የተካተተ ነበር። ዕቅዱ በሁለተኛው የኤኮኖሚ ማሻሻያ  መርሐ-ግብር ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ሲሆን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተጨማሪ የዓለም ባንክ ባለሥልጣናት ጭምር ግፊት የሚያደርጉበት ነው። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “የውጭ ምንዛሪ ግብይት ማሻሻያው እጅግ ጠቃሚ” እንደሆነ እምነት ቢኖራቸውም መንግሥታቸው ሙሉ በሙሉ በገበያ ፍላጎት እንዲመራ ያደርግ እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ዶክተር አብዱልመናን “የኢትዮጵያ መንግሥት እነ አይ.ኤም.ኤፍ. በሚሉት ደረጃ ማድረግም አይችልም፤ አለማድረግም አይችልም። ቢያደርግ የሚያመጣው የኤኮኖሚ ቀውስ በጣም ከባድ ነው። ባያደርግ ደግሞ ከእነ አይ.ኤም.ኤፍ. [ድጋፍ] አያገኝም ማለት ነው” ሲሉ ጉዳዩ ውስብስብ መሆኑን ጠቁመዋል። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ግፊት የኢትዮጵያ መንግሥት የዶላርን የምንዛሪ ተመን አሁን ከሚገኝበት 55 ብር ገደማ በእጥፍ ቢያሳድግ ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት “የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ዕዳ በብር መቶ በመቶ ገደማ ይጨምረዋል።”

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀድሞ እና አዲስ ዋና መሥሪያ ቤቶች
የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክ በሚያደርጉት ግፊት መሠረት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያደርግ ውሳኔ ተግባራዊ ቢያደርግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማትን አደጋ ውስጥ እንደሚጥል የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ያስጠነቅቃሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

“የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ደግሞ ያንን በፍጹም መሸከም አይችልም። በውጭ ምንዛሪ የተበደሩ እንደ ንግድ ባንክ ያሉ ባንኮችን እና ብዙ የመንግሥት ተቋማትን የሚያናጋ ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት [የምንዛሪ ተመኑን በእጥፍ የሚያሳድግ ውሳኔ] ላይስማማ ይችላል” ሲሉ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አስረድተዋል።

መንግሥት አሁን በሥራ ላይ የሚገኘውን ቀስ በቀስ በሽርፍራፊ ሣንቲሞች የሚጨምር የምንዛሪ ተመን በመጠኑ ከፍ በሚያደርግ ውሳኔ ሊስማማ እንደሚችል የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን “እሱም ቢሆን በዚያው ይቆማል ማለት አይደለም። ተጨማሪ ጫና መምጣቱ አይቀርም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግሥት [አንድ ዶላር] በ80 ብር ገደማ እንዲመነዘር ቢስማማ በገበያው ፍላጎት እንዲያደርግ የሚጠይቅ ጫና ይኖራል” ብለዋል።

ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ወደ ውጭ አገራት መላክ የሚጨምረው የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ፈጠራ ዕቅድ

የኢትዮጵያ መንግሥት የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ግብይትን ማስተካከል እና የዕዳ ጫና ማቃለልን የመሳሰሉ ቁልፍ ግቦች ያካተተውን ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍ ተግባራዊ ለማድረግ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 2 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ያቅድ እንጂ ለመጪዎቹ ዓመታት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስፈልገዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሠራው የዕዳ ትንተና ኢትዮጵያ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2026 ባሉት ዓመታት 6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ሬውተርስ ባለፈው ሚያዝያ ከባለሥልጣናቱ ጋር የሚደረገውን ድርድር በቅርበት የሚያውቁ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በመጪዎቹ ሣምንታት ይደረጋል የተባለው ውይይት ተሳክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የጠየቀውን 2 ቢሊዮን ዶላር ቢያገኝ እንኳ ከሚያስፈልገው 4 ቢሊዮን ዶላር ይጎድላል። “ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ምንም አይደለም” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት “በጣም ሰፊ እና ለመፍታት ረዥም ዘመን የሚፈልግ” ሲሉ ይገልጹታል። ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ ብታገኝም የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብሩ “ለማስፈጸም በጣም የሚከብድ” እንደሆነ ዶክተር አብዱልመናን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ