1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦነሠና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስምምነት፤ የታዬ ደንደኣ መፈታት፤ የኤችአይቪ መድኃኒት

ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2017

በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መካከል የሰላም ስምምነት ተደረሰ መባሉ፤ የአቶ ታዬ ደንደአ መፈታት፤ አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ስኬታማ በሆነ መንገድ መሞከሩን ተመራማሪዎች ይፋ ማድረጋቸው ከሰሞኑ መበሠሩ፦ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት ትኩረት ናቸው

https://p.dw.com/p/4no35
AIDS-Aufklärungskampagnen zum Welt-AIDS-Tag
ምስል Saikat Paul/Pacific Press/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት አስተያየቶች

በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መካከል የሰላም ስምምነት ተደረሰ ከተባለ ጥቂት ቀናት ተቆጠሩ ። የቀድሞው የሰላም ሚንሥቴር አቶ ታዬ ደንደአ ደግሞ ትናንት ከእስር ተለቀቁ ተብሎ ወዲያው ሌላ ዜና ተሰምቷል ። ታዬ ትናንት «የፊት ጭምብል ባደረጉ እና በታጠቁ ሰዎች» ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው በነጋታው ዛሬ ደግሞ መፈታታቸው ተዘግቧል ። አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ስኬታማ በሆነ መንገድ መሞከሩን ተመራማሪዎች ይፋ ማድረጋቸው ከሰሞኑ ተበሥሯል ። የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት ትኩረት ናቸው ።

ኦነሰ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስምምነት

በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መካከል የሰላም ስምምነት ተደረገ መባሉ  በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ዘንድ የተለዩ ስሜቶች እንዲንጸባረቁ አድርጓል ። ስምምነቱ መደረሱን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ያሳወቀው እሁድ ዕለት ነበር ። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) በበኩሉ በይፋዊ መግለጫው፦ «መንግስት ከጦሩ የወጡ ግለሰቦች ጋር ያደረገውን ስምምነት ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ስምምነት እንዳደረገ አድርጎ ማቅረቡ አግባብነት የለውም» ብሏል ።

«ከግለሰብ ጋር ስምምነት» ብለውታል አኬል ዳማ ሀገሬ በፌስቡክ አጠር ያለ ጽሑፋቸው ። ብሥራት የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ለሰላም ጊዜው አሁን ነው» ሲሉ በእንግሊዝኛ ጽፈዋል ። አይማን የተባሉ ሌላ ግለሰብ «በስተመጨረሻ ድንቅ ዜና ለኦሮሚያ» ብለዋል በእንግሊዝኛ ጽሑፋቸው ። ሲሣይ ኤም አሞራው ደግሞ፦ «የኦነሰ የጥቃት ዒላማ እና የመከላከያ የድሮን ድብደባ፤ የገፍ እስር ብሎም ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ ፍትህ በሌለበት ኹኔታ አማራን ይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ አድርጎታል» ሲሉ ጽፈዋል ።

የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር ጋር የተደረሰ ስምምነት
የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር ጋር የተደረሰ ስምምነትምስል Oromia communication

ዐሳዬ ደርብ በፌስ ቡክ ጽሑፋቸው፦ «ያን ሁሉ ጭፍጨፋ የፈጸመውና ሸኔ እየተባለ ሲወገዝ የነበረው አሸባሪ ሥሙ ተቀይሮለት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተባለ እኮ» ሲሉ አስፍረዋል ። «እንዳውም አሁን ጥሩ ሆነ ምክንያቱም ቀድመውም አልተጣሉም» ይላሉ ነጋ ተመስገን በዛው በፌስቡክ ። የሪያድ ማኅበረሰብ ድምጽ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «በፈለገ መልኩ ቢሆንም ዋናው ሰላም መስፈኑ ነው» ብለዋል ። ዮኒ የሱ የስቡክ ስም ነው፤ ስምምነቱን፦ «የብልጥግና የጊዜ መግዣ ስምምነት ይባላል» ብለውታል ።

የአቶ ታዬ ደንደአ መፈታት

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ዛሬ ኅዳር 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ከእስር ተለቅቀዉ ከቤተሰባቸዉ ጋር መቀላቀላቸው ተገልጧል ። አቶ ታዬ ትናንት አመሻሹን ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተለቅቀው ቤተሰቦቻቸውን ሳያገኙ ከማረሚያ ቤቱ በራፍ በፀጥታ ኃይሎች ተወስደው እንደነበር ተዘግቧል ።  አቶ ታዬ ዛሬ እኩለ ቀን ደግሞ ሜክሲኮ ከሚገኘው የወንጀል ምርመራ ማዕከል ተለቅቀው ቤታቸው መድረሳቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል ። አቶ ታዬ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድን በይፋ እና በብርቱ ከተቹ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ነበር ለእስር የተዳረጉት

ጽጌሬዳ መራዊ በፌስቡክ ገጻቸው፦ «መከራዉ የበዛ ሰዉ አቶ ታዬ እንኳን ለቤትህ አበቃህ» ብለዋል ። ትእግስት ኃይለማሪያም በበኩላቸው፦ «እሰይ እንኳን ለቤትህ አበቃህ» የሚል መልእክት አስፍረዋል ።  «ንፁሐን የአማራ ፖለቲከኞች ይፈቱ» ያሉት ደግሞ ጌትነት እንዳለው ናቸው ።

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፦ ፎቶ ከማኅደር
የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Million Haileselasi/DW

አቶ ታዬ ትናንት «የፊት ጭምብል ባደረጉ እና በታጠቁ ሰዎች» ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው እንደተሰማ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል ። «እዚያው ቢቆይ ይሻለው ነበር፤ ፈጣሪ ይጠብቀው ፓርላማውና ኢሰመጉ ስለዚህ ምን ይሉን ይሆን ሲሉ ጠይቀዋል ናስር ሞሐመድ በፌስቡክ ። ያብሥራ አሰግድ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «አይ ብልፅግና» ብለዋል በአጭሩ ። «ያዘው ልቀቀው» ሲሉ በአጭሩ የጻፉት መርሻ ተሰማ ናቸው ። «ጥበቃ እየተደረገላቸው ይሆናል» ያሉት ደግሞ መስፍን ማርክ ናቸው በፌስቡክ ። አቶ ታዬ ከእስር ተለቀቁ፤ ጭምብል ባደረጉ ሰዎች ተወሰዱ እንዲሁም እቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር ተቀላቀሉ የሚሉት መረጃዎች የተቀያየሩት ሃያ አራት ሰአታት ባልሞሉ ጊዜያት ውስጥ ነው ። ዛሬ ቤታቸው ደርሰው ከቤተሰብ ጋር መቀላቀላቸው መነገሩን በተመለከተ በርካቶች ፦ «እንኳን ለቤትዎ አበቃዎ» ብለዋል ። 

የኤችአይቪ/ኤድስ ክትባት ግኝት

ከ40 ዓመታት በፊት በዓለም ላይ ለተከሰተው የኤችአይቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ህክምና እና የመከላከያ መድኃኒት ለማግኘት ዓለም ሌት ተቀን ባትሏል ። ጊሊድ የተባለው የአሜሪካ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ አዲስ ውጤታማ የኤች አይ ቪ መድኃኒት ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል ።

ሌናካፓቪር፤ የተባለው አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ ክትባት ስኬታማ በሆነ መንገድ መሞከሩም ተገልጧል ። ተስፋ ሰጪ የተባለው ይህ መድኃኒት በአውሮፓ ኅብረት ጭምር የኤችአይቪ ህሙማንን ለማከም  ፈቃድ አግኝቷል ። በመርፌ መልክ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰጠው ይህ አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት መቶ በመቶ ውጤታማ ነው የመባሉ ዜና  የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ዐቢይ መነጋገሪያ ጉዳይ ሁኗል ።

ሌናካፓቪር፤ የተባለው አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ ክትባት
መቶ በመቶ ስኬታማነቱ ተረጋጋጠ የተባለለት ሌናካፓቪር፤ የተባለ አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ ክትባትምስል Nardus Engelbrecht/AP/picture alliance

የመድኃኒቱ ወይንም ክትባቱ ተገኘ መባል በጥንቃቄ ረገድ መዘናጋት እንዳይፈጥር ባለሞያዎች መክረዋል ። ሊዲያ አማን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ መዘናጋት መኖሩን የሚያመላክተው ጽሑፋቸው፦ «በሽታውን ከመርሳቴ የተነሳ 'ኤድስ' የሚለውን 'አዲስ' ብዬ ነው ያነበብኩት » በሚል ይነበባል ። «መልካም ዜና መስማት ለተጎጂዎች የምስራች ነው » መልእክቱ የሰለሞን ገብረ እግዚአብሔር ነው ።

«በድህነት አዘቅጥ ውስጥ ለምትገኘው  ኢትዮጵያ መዲኃኒቱ በመርፌ መሰጠቱ አጣራጣሪ ነው» ብለዋል ዮማን ዮኒ ። ገብረ እግዚአብሔር ትኩ በበኩላቸው፦ «ዜና ሁኖ እንዳይቀር» ብለዋል ። በአጭር ጽሑፋቸው «ማዘናጊያ» ያሉት የማትበገር ኢትዮጵያ በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ። የኤች አይ ቪ/ኤድስን በመቀነስ ረገድ ባለፉት ዐሥራ አራት ዓመታት እመርታ ካሳዩ ሃገራት ኢትዮጵያም እንደምትገኝበት ይነገራል ።  ኤች አይ ቪ/ኤድስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሽቆለቆለ ነው ቢባልም  ዛሬም መዘናጋት ሳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ  ባለሞያዎች ይመክራሉ ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ