1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኩፍኝ ወረርሽኝ በበርካታ ሃገራት መከሰት

ማክሰኞ፣ የካቲት 5 2016

ካለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 አንስቶ በተለያዩ ሃገራት ኩፍኝ በሽታ መከሰቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ከዚህ ቀደም የነበረው የኩፍኝ ታማሚዎች ቁጥር በ18 በመቶ ከፍ ብሏል።

https://p.dw.com/p/4cMQs
ፎቶ ከማኅደር፤ በሶማሊያ የስደተኞች መጠለያ
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት ኩፍኝ በ10 ሃገራት በርካታ ሰዎችን ይዟል። ፎቶ ከማኅደር፤ በሶማሊያ የስደተኞች መጠለያ ምስል Sun Ruibo/Unicef/Photoshot/picture alliance

የኩፍኝ ወረርሽኝ በበርካታ ሃገራት መከሰት

 

ኩፍኝ ተላላፊ በሽታ መሆኑ ይታወቃል። እናም ያልተከተቡ አስር ሰዎች ለኩፍኝ ተሐዋሲ ቢጋለጡ ዘጠኙ በበሽታው ሊያዙ እንደሚችሉ የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል ሲዲሲ ትናንት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። በተቋሙ ዝርዝር መረጃ መሠረት በአሁኑ ጊዜ ኩፍኝ በስፋት ከተሰራጨባቸው ሃገራት ኢትዮጵያ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እንደተቋሙ መረጃ የመን በአንደኛ ደረጃ፤ ከዚያም አዘርባጃን እና ካዛኪስታን፤ እንዲሁም ህንድ በቅደም ተከተል ከኢትዮጵያ በባሰ መጠን ኩፍኝ ተዛምቶባቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ 10,060 ሰዎች በኩፍኝ መያዛቸውንም ያመለክታል። ዶቼ ቬለ በተለያዩ ጊዜያት ባቀረባቸው ዘገባዎች በተለይ ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ በኩፍኝ በሽታ ሕይወት እየተቀጠፈ መሆኑን አመልክቷል። በዚህ ወቅት ኩፍኝ ለምን ተስፋፋ ያልናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን አሞኘ ያለመከተብ ቀዳሚው ምክንያት ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው።

ኩፍኝ በሽታ አሁን ለምን ተስፋፋ

ኩፍኝ እንዲህ የተስፋፋበት ምክንያትን ሲያመለክትም በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ በመላው ዓለም በተስፋፋባቸው ሁለት ዓመታት ከ61 ሚሊየን በላይ የኩፍኝ ክትባት በተገቢው መንገድ ሳይዳረስ መቅረቱ ነው ብሏል። በወቅቱ ዓለም ትኩረቱን ኮቪድ 19 ላይ አድርጎ በተፈጠረው ግራ መጋባት ክትባቶቹን በየሃገራቱ የማድረሱ ሥራ መስተጓጎሉን በማመልከትም ካለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ወዲህ በየቦታው የኩፍኝበሽታ መከሰቱ እየጨመረ መሄዱንም ጠቁሟል። በአሁኑ ጊዜ የሚታየው በኩፍኝ የሚያያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር በመላው ዓለም በሽታው በወረርሽኝ መልክ የመከሰት ስጋቱን ከፍ ሊያደርገው እንደሚችልም አመልክቷል። አሜሪካንን በሚመለከት ምንም እንኳን ከ23 ዓመታት በፊት ኩፍኝ ሙሉ በሙሉ ከመላው ሀገሪቱ መጥፋቱ ይፋ ቢደረግም በአሁኑ ጊዜ በ31 ግዛቶቿ ከአንድ ሺህ በላይ በኩፍኝ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው መመዝገቡንም አስታውቋል።

የኩፍኝ ክትባት በሰርቢያ
ኩፍኝ የክትባት አቅርቦቱም ሆነ ህክምናው በተዳከመባቸው እንደአፍሪቃና እስያ ባሉ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በአውሮጳና በአሜሪካ ብሎም ብሪታንያ ውስጥም በስፋት መከሰቱ እያነጋገረ ነው። ምስል Jelena Djukic Pejic/DW

ኩፍኝ በሽታ በአውሮጳና ብሪታንያ

ኩፍኝ የክትባት አቅርቦቱም ሆነ ህክምናው በተዳከመባቸው እንደአፍሪቃና እስያ ባሉ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በአውሮጳና በአሜሪካ ብሎም ብሪታንያ ውስጥም በስፋት መከሰቱ እያነጋገረ ነው። ካለፈው ታኅሣሥ ወር ወዲህ ኩፍኝበተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ እስየተስፋፋ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይም ባለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት በኩፍኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ40 በመቶ ከፍ ማለቱን ለዚህም የመከላከያ ክትባት በአግባቡ እየተሰጠ ባለመሆኑ እንደሆነም ተገልጿል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት ኩፍኝ በ10 ሃገራት በርካታ ሰዎችን ይዟል። በጦርነት በደቀቀችው የመን ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች በኩፍኝ የተያዙ ሲሆን በሩሲያም ፌዴሬሽንም የታማሚዎች ቁጥር ከሰባት ሺህ በልጧል። ብሪታኒያ ውስጥም ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ በኩፍኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይፋ ሆኗል። የብሪታንያ የጤና ሚኒስቴር ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ነው ያመለከተው። ኩፍኝ ብሪታንያ ውስጥ ለመስፋፋቱም ክትባቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተገቢው መጠን መከተብ ለሚገባቸው ባለመዳረሱ እንደሆነም ገልጿል። ዶክተር ወንድወሰን ያለመከተቡ መዘናጋት ሰዎች ለክትባት ካላቸው አመለካከት ጋር ያገናኙታል።

በኩፍኝ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ የሚሆነው ያልተከተቡ ሕጻናት እና ያልተከተቡ ነፍሰጡሮችም ጭምር ሲሆኑ በሽታው እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል ነው የሚነገረው። ኩፍኝ ክትባት ያልተከተቡ ብቻ ሳይሆኑ ተከትበው የመከላከል አቅም የሌላቸውንም ሊይዝ እንደሚችለው መረጃዎች የሚያሳዩት።

ክትባት
ኩፍኝ ክትባት ያልተከተቡ ብቻ ሳይሆኑ ተከትበው የመከላከል አቅም የሌላቸውንም ሊይዝ እንደሚችለው መረጃዎች የሚያሳዩት። ምስል Sebastian Barros/NurPhoto/imago images

የኩፍኝ ህመም ምልክቶችና መከላከያ ክትባት

የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች ከሆኑት መካከል ኃይለኛ ትኩሳት፤ የዓይን ቅላትና እንባ ማዘል፤ ሳል እና ማስነጠስ ይጠቀሳሉ። በአፍ ውስጥ ትናንሽ ነጫጭ ሽፍታዎችም ያጋጥማሉ። መላ አካላትን ከማዳረሱ በፊትም ቀላ ያሉ ሽፍታዎች በፊትና ከጆሮ ጀርባ ይወጣል። ምንም እንኳን ኩፍኝ ልጆችን ያጠቃል ቢባልም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን የሚይዝ ተላላፊ በሽታ ነው። ነፍሰ ጡር ሴቶች በኩፍኝ ከተያዙ ለውርጃ ሊዳርግ፤ አለያም ሕይወት አልባ ልጅ እንዲገላገሉ ሊያደርግ እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚገልጹት።

የዓለም የጤና ድርጅት ካለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ወዲህ በኩፍኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ18 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጿል። የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ሁለት ጊዜ መከተብ እንደሚገባ ነው የህክምና መረጃዎች የሚመለክቱት። ክትባቱ ለሕጻናት ከሚሰጡ የተለያዩ በሽታዎችን መከላከያ ከሆኑት አንዱ ሲሆን ዕድሜ ከፍ ብሎም ቢሆን በየትኛው ጊዜ ሊሰች ይችላል። የኩፍኝ ክትባት በተለያዩ ጊዜያት ሆኖም ሁለት ጊዜ መወሰድ እንዳለበት ነው የህክምና መረጃዎች የሚያመለክቱት።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ