1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደመወዛቸው ሊከፈል ይገባል

ቅዳሜ፣ ግንቦት 10 2016

አሁን ላይ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የደሞዝ ጥያቄ በሚያቀርቡ ሠራተኞች ላይ በፀጥታ አባላት እሥር ፣ ወከባና እንግልት እየተፈጸመ ይገኛል ፡፡ ግንባሩ ይህን ድርጊት የሰብአዊ መብት ጥሰት አካል አድርጎ ይመለከተዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4g1wA
የደመወዝ ጥያቄ ያነሱ የዎላይታ ሶዶ የመንግስት ሰራተኞች
የደመወዝ ጥያቄ ያነሱ የዎላይታ ሶዶ የመንግስት ሰራተኞችምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በመንግሥት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸም ማዋከብ እንዲያቆም ተጠየቀ

መንግሥት ፍትሃዊና ህጋዊ ጥያቄ በሚያቀርቡ የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ላይ እየፈጸመ ይገኛል ያለውን ማዋከብ እንዲያቆም የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር / ዎሕዴግ / አሳሰበ ፡፡ ግንባሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በዞኑ ደሞዝ እንዲከፈላቸው በጠየቁ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ የአካባቢው አስተዳደር እሥራትና ድብደባ በማድረስ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት  እየፈጸመ ይገኛል ብሏል ፡፡

የዎላይታ ዞን በንጽጽር የተሻለ የግብር ገቢ ከሚሠበስቡ ዞኖች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ጎኣ “ የሠራተኞች ደሞዝቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ክፍያ መሆን ነበረበት ፡፡ ይህ አለመሆኑ ሠራተኛው ችግር ላይ እንዲወድቅ አድርጓል ፡፡ አሁን ላይ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የደሞዝ ጥያቄ በሚያቀርቡ ሠራተኞች ላይ በፀጥታ አባላት እሥር ፣ ወከባና እንግልት እየተፈጸመ ይገኛል ፡፡ ግንባሩ ይህን ድርጊት የሰብአዊ መብት ጥሰት አካል አድርጎ ይመለከተዋል ፡፡

የደሞዝ ክፍያው ለምን ተስተጓጎለ ?

 ዶቼ ቬለ ለሠራተኞቹ ጥያቄና የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ላወጣው መግለጫ ምላሽ እንዲሰጡት የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላን ጠይቋል ፡፡የሠራተኞቹን ደሞዝ በወቅቱ መክፈል ያልተቻለው በወረዳ የአስተዳደር መዋቅሮች መስፋትና በማዳበሪ ዕዳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የበጀት እጥረት በማጋጠሙ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪ ጠቅሰዋል ፡፡ የሠራተኞች ጥያቄ ትክክለኛና ተገቢ መሆኑን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው “ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመልካም አስተዳደር ተደራሽነትን ለማስፈን ሲባል አዳዲስ የወረዳ መዋቅሮች ተቋቁመዋል ፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዳዲስ ሠራተኞች ቅጥርም ተፈጽሟል ፡፡ ይህ የሆነው ምንም አይነት የበጀት ዕድገት በሌለበት ሁኔታ መሆኑ የዞኑ ዓመታዊ በጀት ላይ ተፅኖ በማሳደር የሠራተኞች ደሞዝ ክፍያ እንዲስተጓጎል አድርጓል “ ብለዋል ፡፡

አቶ ጎበዜ ጎኣ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር
አቶ ጎበዜ ጎኣ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

ቀጣይ መፍትሄ

የዎላይታ ዞን መስተዳድር አሁኑወቅት የሠራተኞቹን የደሞዝ ክፍያ ለመፈጸም አሁን ላይ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ ተናግረዋል ፡፡ ዞኑ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ጥያቄውን ለመመለስ በሚያስችሉ የበጀት አመራጮች ላይ እየተነጋገረ ይገኛል ፡፡ የበጀት ጥቄው እስከ ሰኞ ወይም ከዚያ በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ምላሽ አግኝቶ የደሞዝ ክፍያው እንደሚፈጸም ለመፈጸም እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ ሳሙኤል ጠቅሰዋል ፡፡

 በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የደሞዝ ጥያቄ በማንሳታቸው እሥርና ወከባ ተፈጽሟባቸዋል በተባለው ጉዳይ ላይ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት ዋና አስተዳዳሪው ‘’ ይህ ሀሰት ነው ፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ሠራተኞቹ ሥሜታዊ ቢሆኑም ያቀረቡት የመብት ጥያቄ ነው ፡፡ በሌላ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ደሞዝ በመጠየቃቸው የተዋከቡም ሆነ የታሰሩ  ሠራተኞች የሉም “ ብዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር